Fana: At a Speed of Life!

የኦሮሚያ ክልል ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል – ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ

 
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለአገራዊ ምክክሩ መሳካት አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያደርግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ አረጋገጡ፡፡
 
ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ከአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አባላት ጋር ዛሬ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
 
ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ ኢትዮጵያ በተለያዩ ፈተናዎች ብትፈተንም ችግሮቹን ወደ ዕድል እየለወጠች እንደምትገኝ አስረድተዋል፡፡
 
በቀጣይም የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በሕዝቦቿ አንድነት እና ትብብር በመቅረፍ አመርቂ ውጤት እንደምታስመዘግብም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
 
አገራዊ ምክክሩ በግልጽነት እና በፍትሃዊነት ያለምንም የፖለቲካ ጫና ሕዝቦችን በማሳተፍ መካሄድ እንዳለበትም ነው የጠቆሙት፡፡
 
የኦሮሞ ሕዝብ ሰላም እና ልማት ወዳድ እንደመሆኑ መጠን ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት ከኮሚሽኑ ጎን እንደሚቆም አረጋግጠዋል፡፡
 
አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በበኩላቸው÷አገራዊ ምክክሩ በአገራዊ ጉዳዮች የሕዝቦችን አስተያየት መሰረት በማድረግ ነፃ፣ አካታች እና ታአማኒ በሆነ መልኩ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡
 
ፕሮፌሰር መስፍን በአፋን ኦሮሞ የተተረጎመውን የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አዋጅም ለርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ ማስረከባቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.