Fana: At a Speed of Life!

የክልልነት ጥያቄዎችን የአመጽና የሁከት መነሻ ለማድረግ በሚሞክሩ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ የፌዴራል የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስጠነቀቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልልነት ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኙ ከመንቀሳቀስ ይልቅ ጉዳዩን የአመጽና የሁከት መነሻ ለማድረግ በሚሞክሩ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ፌዴራል የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስጠነቀቀ።
 
የፌዴራል የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ መንግሥት በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱ የክልልነት ጥያቄዎችን በሀገሪቱ ሕግና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየሠራ ይገኛል፡፡
 
ነገር ግን አንዳንድ አካላት ይህንን ሂደት በሚቃረን መንገድ ሕጋዊ ጥያቄዎችን ሽፋን በማድረግ ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር በህቡዕ ዝግጅት ማድረጋቸውን የጋራ ግብረ ኃይሉ ባደረገው ክትትል ስለተደረሰበት ተገቢው እርምጃ ይወሰዳል ነው ያለው፡፡
 
የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት በስሩ የሚገኙ ዞኖችን በአዲስ መልክ ለማዋቀር እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ የጋራ ግብረ ኃይሉ በመግለጫው አመላክቷል፡፡
 
ጌዲኦ ዞንም በአዲስ መልክ ከሚዋቀሩ ዞኖች አንዱ መሆኑን ገልጾ÷ የኅብረተሰቡን ተሳትፎ በተጨባጭ ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ ሰሞኑን የማወያያ ሰነዶች ተዘጋጅተው የዞኑ ነዋሪ እየመከረበት መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
 
ይሁንና የጌዲኦ ዞን የክልልነት ጥያቄ መፍትሔ የማይሰጠው ከሆን ጥያቄያችንን በኃይል እናስፈጽማለን የሚሉ አካላት በህቡዕ ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የፌዴራል የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በተጨባጭ መረጃዎች ማረጋገጡን ነው የተገለጸው፡፡
 
በህቡዕ የተደራጁት አካላት የጥፋት እቅዶቻቸውን ለማሳካት ሀሰተኛ የማህበራዊ ትስስር ገጾች በመክፈት የተዛቡና የፈጠራ መረጃዎችን እያሰራጩ መሆኑን ያመለከተው የጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫ÷ ማኅበረሰቡንም በተሳሳቱ መረጃዎች ለማደናገር እየሞከሩ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
እነዚህ አካላት ያደራጇቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ቤት ለቤት ጭምር እየተንቀሳቀሱ ቅስቀሳ እያደረጉ እንደሚገኙ ይህም በደኅንነትና በጸጥታ አካላት እንደተደረሰበትም አመልክቷል፡፡
 
የጋራ ግብረ ኃይሉ ለዚህ እኩይ ዓላማ የተደራጁና የተሰለፉ ግለሰቦችንና ቡድኖችን በደኅንነትና በጸጥታ መዋቅሩ አማካይነት ለይቶ ክትትል እያደረገባቸው መሆኑን በማስገንዘብ÷ ከጥፋት ተልዕኳቸው እንዲቆጠቡ በጥብቅ አሰስቧል፡፡
 
ይህን ተላልፈው በሚገኙ ላይም ተገቢው ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡
 
አብዛኛው የዞኑ ኅብረተሰብ የጥፋት ተልዕኮ ያነገቡ አካላት ህቡዕ እንቅስቃሴ ተገቢ አለመሆኑን በማመን፥ለጸጥታና ደኅንነት አካላት ጥቆማ በመስጠት የሁከትና ብጥብጥ ተልዕኮው እንዲከሽፍ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም መግለጫው አውስቷል፡፡
 
በቀጣይም ከእንደዚህ ዓይነት የጥፋት ሴራ እራሱን በማቀብ አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት ለመንግሥት አካላት መረጃ በመስጠት የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ የጋራ ግብረ ኃይሉ ጠይቋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.