Fana: At a Speed of Life!

በ10 ዓመታት ተግባራዊ የሚደረገው 2ኛው ብሄራዊ የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ ይፋ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር በሁለተኛው የድርጊት አስር ዓመታት ተግባራዊ እንዲሆን ያዘጋጀውን ብሄራዊ የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ ይፋ አደረገ።

ስትራቴጂው ይፋ በተደረገበት መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ባደረጉት ንግግር፥ የስትራቴጂው ዋና ዋና ምሰሶዎች ከዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎች፣ ስታንዳርዶች እና ከፈረምናቸው ዓለማቀፍ ስምምነቶች እንዲሁም ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እንዲናበቡ ተደርገው ውጤት በሚያመጣ መልኩ የተቀረፁ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የሁሉንም ባለድርሻ አካላት እና አጋር ድርጅቶች ቅንጅታዊ ሥራ የሚጠይቅ በመሆኑ በስትራቴጂው የሰፈሩ ዒላማዎችን እና የድርጊት መስኮችን የሚመለከታቸው ተቋማት ተግባራዊ ሊያደርጓቸው እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡

ሚኒስቴሩ ስትራቴጂውን እና የማስጀመሪያ መርሐ ግብሩን ለማዘጋጀት የብሉምበርግ ኢኒሼቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ አጋር ድርጅት ከሆኑት የዓለም ሀብት ተቋም እና ቫይታል ሰትራቴጂስ የፋይናንስ እና ቴክኒካል ድጋፍ ማግኘቱንም ሚኒስትሯ አንስተዋል፡፡

ስትራቴጂው የአገሪቱን ቀጣይ 10 ዓመት የመንገድ ደህንነት ውጤት የሚወስን ታላቅ ሰነድ እንደመሆኑ፥በመንገድ ደህንነት ላይ የሚተገበሩ ስራዎችን ያካተተ እና ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት አጋዥ የሆነ የስትራቴጂ ሰነድ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚንስትር ዴኤታ አቶ በረኦ ሀሰን በበኩላቸው፥ የትራፊክ አደጋን በተለመደ አሰራርና ባልተቀናጀ አቀራረብ መቀነስ አዳጋች በመሆኑ ስትራቴጂውን ማዘጋጀት እንዳስፈለገ ገልፀዋል፡፡

ስትራቴጂው በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን ሞት በ2030 በ50 በመቶ የመቀነስ ግብ የያዘ ሲሆን÷ ስትራቴጂውን ተግባራዊ ለማድረግ ስድስት የመንገድ ደህንነት ምሶሶዎች ማካተቱን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የመንገድ ደህንነት ተቋማዊ ብቃት እና የአስተዳደር ዘዴ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ ፍጥነት፣ የመንገድ መሰረተ ልማት፣ ተሽከርካሪ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ የመንገድ ተጠቃሚእና ድህረ አደጋ የህክምና አገልገሎት የብሔራዊ ስትራቴጂው ምሶሶዎች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.