Fana: At a Speed of Life!

እድሳት የተደረገለት የስኳር ህክምና ማዕከል ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኘው የስኳር ህክምና ማዕከል ዕድሳት ተጠናቆ ተመረቀ፡

ማዕከሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እና የኢትዮጵያ ስኳር ህሙማን ማህበር፣ ከላየን ክለብ ኢትዮጵያ የሆስፒታሉ አመራሮችና የጤና ባለሙያዎች በተገኙበት  ነው በዛሬው ዕለት የተመረቀው።

ዶክተር ሊያ ታደሰ በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ቅድመ መከላከል እንዲሁም የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት በመስጠጥት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች አንዱ የሆነው የስኳር ህመም ሲሆን በቅድመ መከላከል የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ እንዲሁም ህክምናውን ተደራሽ ለማድረግ አገልግሎቱን በጤና ጣቢያዎች እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸው÷ ይህም በሆስፒታሎች ላይ የሚኖረውን ጫና እንደሚቀንስ ተናግረዋል፡፡

ላየን ክለብ ኢትዮጵያ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ በመግለጽ ለተደረገው የስኳር ህክምና ማዕከሉ እድሳት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በጤና ስርዓቱ የሚታዩ ክፍተቶችን በዘላቂነት ለመፍታት አጋር አካላት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ዶክተር ጌታሁን ታረቀኝ በኢትዮጵያ ስኳር ህሙማን ማህበር ፕሬዚዳንት እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስኳር ህክምና ክፍል ሀላፊ እንደገለጹት÷ ማዕከሉ ለባለፉት 28 ዓመታት ለስኳር ህክምና አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

ማዕከሉ ከሁሉም ክልሎችና አካባቢዎች በሪፈራል የሚላክበት በመሆኑን በቀን ከአንድ መቶ ሀምሳ በላይ ታካሚዎች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.