Fana: At a Speed of Life!

የነዋሪውን የቤት ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየሠራን ነው- ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ቤቶችን ማደስ እና በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቁ ቤቶችን በመገንባት የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

ወደፊትም በሌሎች አማራጮች የነዋሪውን የቤት ችግር ለመቅረፍ እንሠራለን ብለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች የተገነባ የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ በማውጣት ርክክብ ተደርጓል፡፡

ነዋሪዎቹ ቀደም ሲል “በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ቤታቹ ትገባላችሁ” በሚል በጊዚያዊ መጠለያ ለረጅም ጊዜ በከፍተኛ ችግር እንዲቆዩ መደረጉን ለጣቢያችን አመልክተው የነበረ ሲሆን፥ ፋና ቴሌቪዥንም የነዋሪዎቹን ቅሬታ በመያዝ በተባለለት ጊዜ መጠናቀቅ ያልቻለውን የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ በተመለከተ ተከታታይ ዘገባዎች መስራቱ ይታወሳል።

ቤቶቹን÷ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ መርቀው አስረክበዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቤቶቹ ምረቃና ርክክብ ስነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር በከተማዋ የቤት ጉዳይ አንገብጋቢ መሆኑን ጠቁመው÷ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ቤቶችን ማደስ እና በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቁ ቤቶችን በመገንባት ችግሩን ለማቃለል እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የቤት ግንባታው ከተያዘለት ጊዜ በመዘግየቱ ነዋሪዎች ቅሬታ እና ጥርጣሬ ውስጥ ገብተው እንደነበር ገልጸው÷  “እኛ የሕዝብን አደራ አንበላም፤ ይኸው ተጨማሪ አስር ሰዎችን መያዝ በሚችል መልኩ ግንባታቸው ተጠናቋል” ብለዋል።

ወደፊትም በሌሎች አማራጮች የነዋሪውን የቤት ችግር ለመቅረፍ እንሠራለን ብለዋል።

አሁን 29 አባዎራዎችን መያዝ የሚችለው የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታው ተጠናቆ 19 ነዋሪዎች እጣ በማውጣት ቁልፍ ተረክበዋል።

በዘመን በየነ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.