Fana: At a Speed of Life!

ድሬዳዋን ከጎርፍ አደጋ ለመታደግ ችግኞችን መትከልና መንከባከብ የነዋሪዎቿ ሃላፊነት ሊሆን ይገባል -አቶ ከድር ጁሃር

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ድሬዳዋን ከጎርፍ አደጋ ለመከላከል እና የምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል ምቹ የመኖሪያ ስፍራ ለማድረግ ችግኞችን ተክሎ መንከባከብ ላይ መረባበረብ የነዋሪዎቿ ትልቅ ሃላፊነት ነው ሲሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር ተናገሩ።

ከንቲባው ይህን የተናገሩት ” ዐሻራችን ለትውልዳችን” በሚል መሪ ሃሳብ አራተኛው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መረሃ-ግብርን በድሬደዋ ባስጀመሩበት ወቅት ነው፡፡

ከንቲባ ከድር አዳዳ ገጠር ቀበሌ ላይ ስነ ስርአቱን የተለያዩ የጥላ እና የፍራፍሬ ችግኞች በመትከል መረሃ-ግብሩን ያስጀመሩ ሲሆን÷ የገጠሩን ማህበረሰብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያከናውናቸው ስራዎች ፍሬያማ የሚሆኑት የተተከሉትን የፍራፍሬ ችግኞች በአግባቡ በመንከባከብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የድሬደዋ አስተዳደር የግብርና ውሃ ማዕድን ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ በበኩላቸው÷ ከሚተከሉት ችግኞች መካከል 660 ሺህዎቹ ለምግብነት የሚያገለግሉ ፍራፍሬዎች ናቸው ብለዋል፡፡

ዛሬ በተጀመረውና ክረምቱን በከተማ እና በገጠር ተጠናክሮ በሚቀጥለው የአራተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ሁለት ሚሊየን አገር በቀል የጥላ ፣የውበት እና የፍራፍሬ ችግኞች እንደሚተከሉ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በ38 ሄክታር የተራቆተ መሬት ላይ የሚተከሉትን ችግኞች አንድ መቶ የተደራጁ ወጣቶች ክብካቤ እና ጥበቃ እንደሚደረግላቸውም ተመላክቷል፡፡

በመርሐ ግብሩ የድሬደዋ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ፈቲህያ አደን፣የድሬደዋ የብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ እና የካቢኔ አባላት ተሳትፈዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.