Fana: At a Speed of Life!

በዛምቢያ ሉሳካ ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ ኀብረት የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዛምቢያ መዲና ሉሳካ ሲካሄድ የነበረው የአፍሪካ ኀብረት የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል፡፡
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በሥራ አስፈፃሚው መደበኛ ስብሰባው ላይ ተሳትፎ ወደ አገሩ ተመልሷል።
የሥራ አስፈፃሚው ምክር ቤት ስብሰባ፥ የአፍሪካ ኀብረት የ2023 በጀት 654.8 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እንዲሆን የጸደቀ ሲሆን፥67 በመቶው በአጋሮች እንደሚሸፈን ተገልጿል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበጀት ማፅደቁ ሂደት ለሰላም ማስከበር የሚውለው በጀት ሙሉ በሙሉ በዓለም አቀፍ አጋሮች እንዲሸፈን መደረጉ አጋግባብ አለመሆኑን አንስተዋል።
ቁልፍ ለሆነው የሰላም ጉዳይ ከሚውለው በጀት በቀጣይ ቢያንስ አብላጫውን አህጉሪቱ በራሷ መሸፈን እንዳለባት ያስገነዘቡት አቶ ደመቀ ፥ ሀሳቡን ሌሎች በርካታ ተሳታፊ ሀገራት ደግፈውታል።
ኢትዮጵያ አፍሪካን በመወከል የዐለም አቪዬሽን ድርጅት ምክር ቤት አባል ሆና እንድታገልገል በመደበኛ ስብሰባው በእጩነት የቀረበች ሲሆን፥ ምክር ቤቱ እጩነቷን በሙሉ ድምፅ ተቀብሎ አፅድቆታል።
የአፍሪካ የህብት ሪፎርምን አመልክቶ የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤቱ የኀብረቱን የሰራተኞች አስተዳደር ሁኔታ በስፋት ተመልክቶታል።
በዚህም አብዛኛው የኀብረቱ ሰራተኞች በጊዜያዊ ኮንትራት የተቀጠሩ መሆኑ ተጠቅሶ፥ ይህም መቀየር እንዳለበት መግግባት ላይ ተደርሷል።
በቅርቡ ለተመሰረተው የአፍሪካ መድሃኒቶች ኤጀንሲ ዋና መቀመጫ አስተናገጅ ሀገር መምረጥ የ41ኛው የኀብረቱ
የአስፈፃሚ ምክር ሌላው አጀንዳ የነበረ ሲሆን፥ ሩዋንዳ አሸናፊ በመሆን የኤጀንሲው መቀመጫ ሆና ተመርጣለች።
በዛምቢያ መዲና ሉሳካ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ በቆየው የአፍሪካ ኀብረት የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ሲሳተፍ የነበረው በአቶ ደመቀ መኮንን የተመራው ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ መመለሱንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.