Fana: At a Speed of Life!

የገቢዎች ሚኒስቴር እና ጉምሩክ ኮሚሽን ለደቡብ ምዕራብ ክልል ከ53 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር እና ጉምሩክ ኮሚሽን ለተለያየ አገልግሎት የሚውል ከ53 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የገንዘብ እና የዓይነት ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር እና ጉምሩክ ኮሚሽን አመራሮች እና ሠራተኞች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ካፋ ዞን ዋቻ ከተማ የ4ኛውን ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካሂደዋል፡፡
ከችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ባሻገርም ለተቸገሩት ወገኖች የሚውል ከ32 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የአልባሳት ድጋፍ አድርገዋል።
እንዲሁም ለክልሉ ማጠናከሪያ የሚሆን 10 ሚሊየን ብር እና ለክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚውል 5 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡

በተጨማሪም በካፋ ዞን ዋቻ ከተማ ለቦባ ቆጫ ትምህርት ቤት ጥገና የሚውል የ6 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የተፈጥሮ ሃብታችንን ጠብቆ ማልማት ይገባል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

ትምህርት ቤቶች ተተኪ ዜጎችን የምናፈራበት በመሆኑ ትውልዱን ለመንከባከብ የሚያስችል ድጋፍ አድርገናልም ነው ያሉት፡፡

የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ በበኩላቸው÷ ተቋሙ ከዚህ ቀደምም ክልሉን በመርዳት ቀዳሚ መሆኑን ጠቅሰው አሁን ለተደረገው ድጋፍም አመስግነዋል።

ክልሉ በርካታ የወጪ ምርቶችና ማዕድናት የሚገኝበት በመሆኑ ሚኒስቴሩ በክልሉ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ ጠይቀዋል፡፡

የተሰጡንን ድጋፎች ለታለመለት ዓላማ አውለን ችግኞችንም ተንከባክበን ዕቅዳችንን ፍሬያማ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.