Fana: At a Speed of Life!

የምዕራባውያን የበላይነት እያከተመ ነው – ቶኒ ብሌየር

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የምዕራቡ ዓለም የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ የበላይነት አክትሞ ከምሥራቁ ጋር እኩል የሚወስኑበት ጊዜ ላይ መደረሱን የቀድሞው የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ቢሌየር አስታወቁ፡፡

ብሌየር አክለውም÷ የአሜሪካ እና አጋሮቿ ዓለም አቀፋዊ የበላይነት እያከተመ መሆኑን ያላቸውን ምልከታ ትናንት በ “ዲችሌ ፋውንዴሽን” ዓመታዊ የጥናት ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግራቸው አንጸባርቀዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የምዕራቡ ዓለም ሀገራት ኢኮኖሚ እንደተቀዛቀዘ እና በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል የዘለቀው ጦርነት መባባስ በመሰረታዊ ፍጆታ እና የኃይል አቅርቦት ላይ እክል በመፍጠሩ ምክንያት ምዕራባውያኑን አንገዳግዶ ሚዛናቸውን እንዳሳተ እና ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖውን እንዳሳረፈም አስረድተዋል፡፡

የምዕራቡ ዓለም ፖለቲካ ግራ እንደተጋባና በማኅበራዊ ሚዲያ ረብ የለሽ አሉባልታ እንደተቃኘም ነው ያወሱት፡፡

ቶኒ ብሌየር ÷ የምዕራባውያኑ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ሩሲያ በዩክሬን ላይ በፈጸመችው ወታደራዊ ዘመቻ ጉዳይ ላይ በሚወስኗቸው ውሳኔዎች ሊለካ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡

የምዕራባውያኑ ቀጣይ ተግዳሮት የዓለም ሁለተኛዋ ልዕለ-ኃያል ሀገር ቻይና እንደሆነች እና ከሩሲያ ጋር የምዕራቡን ዓለም የኃይል ሚዛን ብቻ ሳይሆን የስተዳደር ሥርዓት እና አኗኗር ሁሉ እንደሚያፋልሱት ባደረጉት ንግግር ማስገንዘባቸውንም አር ቲ ኒውስ ዘግቧል፡፡

የዲችሌይ ዓመታዊ የጥናት ጉባዔ ÷ በዋናነት በብሪታኒያ እናአሜሪካ ግንኙነት ላይ በማተኮር የሚካሄድ ሲሆን÷ ፋውንዴሽኑ የሚገኘውም በቺፕንግ ኖርተን፣ ኦክስፎርድሻየር አቅራቢያ በዲችሌይ ፓርክ ነው።

የ69 ዓመቱ ቶኒ ብሌየር ከፈረንጆቹ 1997 እስከ 2007 ብሪታኒያን በጠቅላይ ሚኒስትርነት መምራታቸው ይታወሳል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.