Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት በትኩረት እየሠራች ነው -ገንዘብ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ነው ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰመሪታ ሰዋሰው ተናገሩ፡፡
በ14ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ኮሚቴ ስብሰባ እየተሳተፉ የሚገኙት ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው÷ ኢትዮጵያ ለዘላቂ ልማት ግቦች መሳካት ልዩ ትኩረት የምትሰጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ ከፍተኛ የዋጋ ንረት፣ የአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል እና ጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች መጨመር እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ በሀገሪቱ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሁሉንም ተግዳሮቶች በመጋፈጥ የረጅም ጊዜ የልማት ፍላጎቶቿን ለማሳካት የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ ተግባራዊ እያደረገች እንደምትገኝ መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማት ላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት አበረታች ሥራዎችን እያከናወነች መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ÷ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ባለፉት አራት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 18 ቢሊየን ችግኞች እንደተተከሉም አስረድተዋል፡፡
ከ2030 አጀንዳዎች ውስጥ ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጣቸው እና በዘላቂ የልማት ግቦች ላይ የተካተቱት የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይም ኢትዮጵያ በትጋት እየሠራች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.