Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባን ሠላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ የሚያከናውነውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ግብረ ሃይሉ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ እና ዙሪያውን ሠላምና ፀጥታን ለማስጠበቅ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል የሚያከናውነውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡

ህብረተሰቡም ለፀጥታ አካላት የሚደርገውን ቀና ተባባሪነት አጠናክሮ እንዲቀጥል የጋራ ግብረ-ሃይሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የጋራ ግብረ-ኃይሉ ዛሬ ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል ፦

ባለፉት ተከታታይ የለውጥ ዓመታት የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን አዲስ አበባ እና ዙሪያውን የሁከትና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ ያላቀዱት ዕቅድ ያልሞከሩት ሙከራ እንዳልነበረ ከሰላም ወዳዱ ህዝባችን የተሰወረ አይደለም፡፡ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ልዩ ልዩ የግጭት አጀንዳዎችን በመቀረፅ ሰላምና ደህንነት ለማደፍረስ ቢንቀሳቀሱም ሰላም ወዳዱ ህዝባችን እያደረገ ባለው ያላሰለሰ ድጋፍ እና በፀጥታ አካላት ጠንካራ ርብርብ በተለያዩ ጊዜያት በፀረ-ሰላም ሃይሎች የተጎነጎኑ ሴራዎች ከሽፈዋል፡፡

በፀጥታና የደህንነት የጋራ ግብረ ሃይሉ በአዲስ አበባ እና ዙሪያው ቀደምሲል በተከናወኑ የጥፋት ተልዕኮን የማክሸፍ ተግባር ከ5 ሺ በላይ የብሬን ጥይቶችን በርካታ ክላሽን ኮቭ ጠብመንጃዎች ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎች፤ ተቀጣጣይና ተተኳሽ ፈንጂዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን ፡በጨማሪም በቅርቡ የፀጥታና የደህንነት የጋራ ግብረ ሃይሉ ባከናወነው የቅድመ ወንጀል መከላከል ተግባሩ መነሻቸውን ከተለያዩ የሀገራችን ክልሎች ባደረጉ ተሸከርካሪዎች የውስጥ አካላት ተሸሽጎ የገባ ከ10 ሺ በላይ የሽጉጥ ጥይቶች ከሰባት ተጠርጣዎች ጋር ተይዘው ምርመራው እየተደረገባቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡

በተመሳሳይ ባለፉት አስራ አምስት ቀናቶች በጥምር የፀጥታ አካላት በተከናወኑ የጥፋት ተልዕኮን የማክሸፍ ተግባር በርካታ የብሬን ጥይቶች ፤17 ሽጉጥ ከ107 መሰል ጥይቶች ፤ የተለያዩ የነፍሰ ወከፍ መሳሪያዎች ከመሰል ጥይቶች ጋር 10 ላፕቶፖችን ጨምሮ ልዩ ልዩ ኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች ፤ የተለያዩ ወታደራዊ አልባሳቶችና ቁሳቁሶች ከበርካታ ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ሥር ሲውሉ በተመሳሳይ ቤት ለቤት በተደረገ አሰሳና ፍተሻ 27 ሽጉጦች ከ1239 መሰል ጥይቶችጋር 3 ክላሽን-ኮቭ ከ88 መሰል ጥይቶች ጋር ዲጂታል ካሜራዎች እና ልዩ ልዩ ሰነዶች በፀጥታ ሃይሉ ተይዘዋል፡፡ በእግረኛና በተሽከርካሪ ላይ በተደረገ ድንገተኛ አሰሳና ፍተሻም የተለያዩ ድምፅ አልባ መሳሪያዎች እና ሽጉጦች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፥ የአሸባሪው የህወሀት ጁንታ ቡድን ተላላኪ የሆነው ሸኔ በኦሮሚያ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የፈፀማቸውን እኩይ ተግባራት በአዲስ አበባ እና በዙሪያው ባሉ ከተሞች ለመድገም ያለውን ፍላጎት በጦር መሳሪያና በወታደራዊ ግብዓቶች አጠናክሮ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ቢያደርግም ሰላሙን እንደ ዓይኑ ብሌን በሚጠብቀው የፀጥታ መዋቅርና በነዋሪው ቀና ተባባሪነት ሙከራዎቹ ሁሉ እየከሸፈ እና ለዚሁ የጥፋት ዓላማ የተሰማሩ ሃይሎችም በቁጥጥር ስር እየዋሉ ይገኛል፡፡ የውጭና የውስጥ ተላላኪ ጠላቶቻችን የጥፋት ፉከራቸውን በሚያዳምቁላቸው ልዩ ልዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች እየታገዙ ፖለቲካዊና ሐይማኖታዊ አጀንዳዎችን በማደበላለቅና ህዝብን በማነሳሳት ተልዕኳቸውን ለማሳካት የኖሩበት ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ፀረ-ሰላም ቡድኖች በህዝቦች መካከል የተለያዩ የጥላቻና የልዩነት ወሬዎችን በማናፈስ ህዝብ በህዝብ ላይ እንዲነሳ ልዩ ልዩ ሴራዎችን ሸርበው እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ለሁሉም ግልፅ ነው፡፡

መንግስት እየወሰደ ያለው ህጋዊ እርምጃ ውጤታማ እንዲሆን የነቃ የህዝብ ተሳትፎ ወሳኝ ስለሆነ ህብረተሰቡ አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅ እና አጠራጣሪ ጉዳዩች ሲያጋጥሙት ለፀጥታ አካላት መረጃ የመስጠት ልምዱን አጠናክሮ እንዲቀጥልበተለይ የመኖሪያና የንግድ ቤት፣መጋዘን እና ተሽከርካሪ የሚያከራዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች የተከራዮችን ማንነት በጥንቃቄ በማጣራት መረጃውን ለፀጥታ አካላት በማሳወቅ የዜግነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የፀጥታና የደህንነት የጋራ ግብረ ሃይሉ ያሳስባል፡፡የአዲስ አበባ እና የዙሪያውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በሽብር ቡድኖቹ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ግብረ ሃይሉ እያስታወቀ ሀሰተኛና የተዛባ መረጃ የሚያስተላልፉ እና የሚያስተጋቡ አካላት ከህገወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጥብቅ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡

ህብረተሰቡም በአካባቢው የተሰገሰጉ ከየት እንደመጡና ማንነታቸው የማይታወቁ ግለሰቦችን በመለየት እና አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት ወይም የፖሊስ አገልግሎትን ማግኘት ሲፈልግ በፌዴራል ፖሊስ 987 እና በአዲስ አበባ ፖሊስ 991 ነፃ የስልክ መስመር መጠቀም እንደሚችል የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረኃይል ጥሪውን ያስተላልፋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.