Fana: At a Speed of Life!

በሶማሌ ክልል ለ2015 በጀት አመት የታቀዱ የልማት እቅዶች እንዲሳኩ በየደረጃው ያለው አመራር የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል መንግሥት ለ12 ቀናት በጅግጅጋ ከተማ ሲያካሂድ የነበረውን የ2014 ዓ.ም የመንግሥት ሴክተር መሥሪያ ቤቶች የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ የተለያዩ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ዛሬ ከቀትር በኋላ አጠናቀቀ።

ግምገማው በክልል፣ በዞንና በከተማ አስተዳደር ደረጃ በመክፈል የተካሄደ ሲሆን፥ ሁሉም የክልሉ መስሪያቤቶች፣ 11 ዞኖችና 6 የከተማ መስተዳደሮች የአፈፃፀም ሪፖርታቸውን በማቅረብ ተገምግሟል።

ሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ኡስማንና የክልሉ ብልፅግና ፅህፈት ቤት ሀላፊ ኢ/ር መሀመድ ሻሌ በተገኙበት ተገምግመዋል።

ሴክተር መሥሪያ ቤቶቹ በበጀት ዓመቱ ያቀዱትን እቅዶችና በተለይ በፕሮጀክቶች አፈፃፀም፣ በበጀት አጠቃቀም፣ በአገልግሎት አሰጣጥና በድርቅ አደጋው ምላሽ ባከናወኑት ስራዎች ላይ ሪፖርታቸውን ያቀረቡ ሲሆን፥ በቀረበው ሪፖርት ላይም ሰፊ ውይይቶችና ክርክሮች በማድረግ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።

ግምገማው መጠናቀቁን ተከትሎ የመዝግያ ንግግር ያደረጉት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ፥ “በግምገማው ከየት እንደተነሳንና አሁን ያለንበት ደረጃ እንዲሁም የወደ ፊት አቅጣጫችንን ያወቅንበት ነው” ብለዋል።

በአጠቃላይ በ2014 በጀት ዓመት በክልሉ በርካታ አመርቂ ስራዎች መሠራታቸውን ማየት ተችሏልም ነው ያሉት።

አክለውም በበጀት ዓመቱ ውጤቶች ከተገኘባቸው ስራዎች መካከል የድርቅ አደጋውን ለመቀልበስ የተሰራው ሥራና የተገኘው ውጤት ከፍተኛ እንደነበር ተናግረው፥ አመራሩ በበጀት አመቱ መስተካከል አለባቸው የተባሉት ዘርፎች በማስተካከል በአዲሱ የ2015 በጀት አመት ላይ የታቀዱ የልማት እቅዶች እንዲሳኩ በየደረጃው ያለው አመራር የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

የዘንድሮው የ2014 ዓ.ም የመስሪያ ቤቶች የአፈፃፀም ሪፖርት ከወትሮው የተለየ ነበር ያሉት አቶ ሙስጠፌ፥ ሁሉንም የግምገማው ሂደት ህዝቡ በሚዲያ በየቀኑ እንዲከታተል መደረጉ፣ ህዝቡ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት እንዲጨምር አድርጓል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ።

በቀጣይ የ2015 ዓ.ም በጀት አመት ላይ በሁሉም የክልሉ የመንግሥት መዋቅር ላይ ወጪዎችን በመቀነስና እንደ ሀገርና እንደ ክልል የተያዘውን ኢኮኖሚን የማረጋጋት ሥራን ሁሉም አመራር የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

በግምገማው ማጠቃለያ ላይ የሶማሌ ክልል መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ኡስማን በበኩላቸው፥ በበጀት ዓመቱ ክፍተቶች አሉ ተብለው የተለዩ ስራዎች እና ሴክተሮች ላይ በተለይ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ክትትል እንዲደረግ፣ እንዲሁም ለህዝቡ የሚሰጠው የአገልግሎት አሠጣጥን በፍጥነት እርማት በመስጠት ለቀጣይ ሥራ አመራሩ ዝግጁ መሆን አለበት ብለዋል።

አክለውም በቀጣይ በጀት አመት በገቢ ግብር አሰባሰብ ላይ በስፋት በመስራት የክልሉ ገቢ ማደግ አለበት ብለው፥ የለውጥ ስራዎችንም ተግባራዊ በማድረግ ሁሉም ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በጋራና በቡድን የመስራት ባህልን እንዲያዳብሩ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.