Fana: At a Speed of Life!

በበጀት ዓመቱ ከ15 ሺህ 400 ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ ኃይል ማመንጨት መቻሉን የኤሌክትሪክ ኃይል ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2014 በጀት ዓመት ከ15 ሺህ 400 ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ ኃይል ማመንጨት መቻሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለጸ፡፡

በተቋሙ የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው÷በ2014 በጀት ዓመት 17 ሺህ 953 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ታቅዶ 15 ሺህ 487 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ማመንጨት ተችሏል፡፡

14 ሺህ 900 ነጥብ 27 ጊጋ ዋት ሰዓት ከውሃ፣ 557 ነጥብ 66 ጊጋ ዋት ሰዓት ከንፋስ እንዲሁም 29 ነጥብ 2 ጊጋ ዋት ሰዓት ከእንፋሎት በማመንጨት የዕቅዱን 86 በመቶ ማሳካቱን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል፡፡

ባጋጠመው የፀጥታ ችግር ምክንያት በመሰረተ ልማቶች ላይ በደረሰ ጉዳት የኃይል ተጠቃሚ ቁጥር በማነሱ በዕቅዱና በአፈፃፀሙ መካከል የ2 ሺህ 466 ጊጋ ዋት ሰዓት ልዩነት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗልም ተብሏል፡፡

በበተከዜና አሸጎዳ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ እንዲሁም በገናሌ ዳዋ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ በካሳ ክፍያ ጥያቄ ምክንያት የታቀደውን ያህል ኃይል ማምረት እንዳልተቻለም ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡

የ2014 በጀት ዓመት የኃይል ምርት ከ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ300 ጊጋ ዋት ሰዓት ቅናሽ ማሳየቱም ነው የተገለጸው፡፡

በስራ ላይ ከሚገኙት 19 የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ውስጥ ጊቤ 3ኛ፣ መልከ ዋከና፣ ፊንጫ፣ ጢስ አባይ 2ኛ፣ አዋሽ 2ኛ እና 3ኛ እንዲሁም አዳማ 2 የኤሌክትሪክ ማመንጫ ጣቢያዎች ከታቀደላቸው በላይ ኃይል ማመንጨታቸው ተጠቅሷል።

አመርቲ ነሼ፣ ጊቤ 1 እና 2፣ ጣና በለስ፣ ቆቃ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችና አዳማ 1 የንፋስ ማመንጫ ጣቢያ ያመነጫሉ ተብሎ ከታቀደላቸው በታች ያመነጩ ጣቢያዎች መሆናቸውን ከኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.