Fana: At a Speed of Life!

የቀጠለውን የአሸባሪዎቹን የወያኔ እና የሸኔ ጋብቻ ያጋለጠው ቃለ መጠይቅ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ)  የአሸባሪዎቹ የህወሓት እና ሸኔ ያልተቀደሰ ጋብቻ አሁንም የቀጠለ መሆኑን ያጋለጠ ቃለ መጠይቅ በቅርቡ በአንድ የወያኔ ጉዳይ ፈፃሚ የሆነ የኦን ላይን ሚዲያ ተካሂዷል፡፡

 

በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጁት ህወሓት እና ሸኔ ኢትዮጵያን ለማዳከም እና ለማፈራረስ፥ ሕዝቦቿንም ለማጫረስ ያልተቀደሰ ጋብቻ በመፈጸም በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን አገራችንና የቁርጥ ቀን ልጆቿ “ዘመቻ ለኀብረ ብሔራዊ አንድነት”ን ባጠናከሩበት ወቅት በግልጽ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

 

አሸባሪ ቡድኖቹ ለዚህ እኩይ ዓላማቸው መሳካትም በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በአሰቃቂ ሁኔታና ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ ንጹሐን ዜጎችን ከመጨፍጨፍና ከማስጨፍጨፍ የዘለለ ዓላማ እና ግብ የሌላቸው ስብስቦች እንደሆኑ በግልጽ አሳይተዋል፡፡

 

በተለይም አሸባሪው ህወሓት ላለፉት ዓመታት ኢትዮጵያን ለማዳከም እና የራሱን የቅዠት እቅድ ለማሳካት አሸባሪው ሸኔን የእኩይ ምግባሩ ማስፈጸሚያ መሳሪያ አድርጎ ሲጠቀምበት እንደነበር መንግስት በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡

 

ሰሞኑን ራሱን የሸኔ መሪ ነኝ ብሎ የሚገልጸው ጃል መሮ ከአንድ የወያኔ ጉዳይ ፈጻሚ ከሆነ የኦንላይን ሚዲያ ጋር በቅርቡ ያደረገው ቃለ መጠይቅም የሽብር ቡድኖቹ አሁንም አገርን ለማፍረስ የፈጸሙት ስምምነት እና ሴራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያጋለጠ ነው፡፡

 

ጃል መሮ ከኦንላይን ሚዲያው ጋር በነበረው ቆይታ “ድርጅታችሁ (ሸኔ) ከህወሓት ጋር ያለው ግንኙነት እንደቀጠለ ነው? አሁንም በጋራ እየሰራችሁ ነው ወይ?” የሚል ጥያቄ  ቀርቦለታል፡፡

 

ጃል መሮ በሰጠው ምላሽ “ከህወሓት እና ከሌሎች አጋር ፓርቲዎች ጋር የመሰረትነው ህብረት አሁንም እደቀጠለ ነው ” ሲል አረጋግጧል፡፡

 

ጃል መሮ በቃለ መጠይቁ ከወያኔ ጋር ተባብሮ እንደሚሰራና በየአካባቢው የጥፋት ሃይሉ እንደተሰማራ በአንድ በኩል እየተናገረ፥  በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል ብሎም በሌሎች አካባቢዎች የአሸባሪው ሸኔ ታጣቂዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸሙትን ገሃድ የወጣ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ለመካድ ሞክሯል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.