Fana: At a Speed of Life!

አቶ ተወልደ ገ/ማርያም የህይወት ዘመን ሽልማት ተበረከተላቸው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቀድሞ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገ/ማርያም በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ላሳዩት የላቀ አመራር ፍላይት ግሎባል የተሰኘ የእንግሊዝ ኩባንያ የህይወት ዘመን ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡

ፍላይት ግሎባል “ኤርላይን ቢዝነስ ” የተሰኘ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን መጽሔት አሳታሚ ኩባንያ ሲሆን ከፈረንጆቹ 2002 ጀምሮ ” ኤርላይን ስትራቴጂ አዋርድ ” በየዓመቱ በማዘጋጀት ለአየር ትራንስፖርት ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ላደረጉ ግለሰቦችና ኩባንያዎች እውቅና ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

አቶ ተወልደ የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ለንደን በተዘጋጀው የሽልማት ፕሮግራም ላይ መቀበላቸውን ከኢትዮ ንግድና ኢንቨስትመንት መድረክ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ፍላይት ግሎባል ባወጣው መግለጫ አቶ ተወልደ ገ/ማርያም የተሸለሙት የኢትዮጵያ አየርመንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው ባገለገሉባቸው 11 ዓመታት ላሳዩት የረጅም ጊዜ መርሐ ግብር እቅድ ዝግጅትና ቀውስን የመቆጣጠር ክህሎት እውቅና ለመስጠት እንደሆነ አስታውቋል፡፡

በእርሳቸው አመራር አየርመንገዱ በአራት እጥፍ ማደጉን ፍላይት ግሎባል የጠቀሰ ሲሆን ፥ የኢትዮጵያ አየርመንገድ የአውሮፕላን ብዛት ከ33 ወደ 130 ፣የመንገደኞች ቁጥር ከ3 ሚሊየን ወደ 12 ሚሊየን እንዳደገ ኩባንያው ጠቁሟል፡፡

አቶ ተወልደ አየርመንገዱን ለ37 አመታት ካገለገሉ በኋላ ባለፈው የካቲት ወር ከጤና ጋር በተያያዘ ከሃላፊነታቸው መልቀቃቸው ይታወሳል፡፡

ዕውቅና በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ የገለጹት አቶ ተወልደ ፥ “የሽልማት ፕሮግራሙን ላዘጋጁት ፍላይት ግሎባል አስተዳደርና ሰራተኞች እንዲሁም በኢትዮጵያ አየርመንገድ ባገለገልኩበት ወቅት አብረውኝ ለደከሙ ባልደረቦቼ በሙሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ” ብለዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.