Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ውጥረት እያባባሰች ነው አለች ኢራን

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ያልተሳካላትን ኢራን-ጠል ፖሊሲዋን መሰረት በማድረግ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ውጥረት እያባባሰች ነው ሲል የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ሰሞኑን በቀጠናው ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ በሰጡት አስተያየት፥ አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ “የከሸፈ” ያሉትን ኢራን – ጠል ፖሊሲዋን በማራመድ ውጥረቶችን ለመፍጠር እየጣረች ነው ብለዋል።

“አሜሪካ የኒውክሌር ቦምብ በአካባቢው በማስማራት የመጀመሪያዋ ሀገር ነች” ያሉት ባለስልጣኑ፥ “ያለማቋረጥ በሌሎች ሀገራት ጉዳዮች ጣልቃ ትገባለች ፣ በትጥቅ የታገዙ ግጭቶችን ትከፍታለች እንዲሁም በቀጠናው ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያ ትሸጣለች” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዋሽንግተን ለእስራኤል በምታደርገው ያልተቋረጠ ድጋፍ የፍልስጤም መሬቶች ለቀጣይ ወረራ እንዲዘጋጁ፣ በፍልስጤማውያን ላይ የሚፈፀሙ የየዕለት ወንጀሎች እና የዘር ጭፍጨፋ እንዲባባስ እያደረገ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

የኢራን ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲ አሜሪካና አጋሮቿ ኢራንን አስመልክቶ በሚያደርጉት ግንኙነት ዳግም ስህተት ከሰሩ የከፋ ምላሽ እንደሚሰጡ የዛቱ ሲሆን፥ ዋሽንግተን እና እስራኤል በአካባቢው አለመረጋጋት እንዲፈጠር እያደረጉ ነው ሲሉም ከሰዋል።

የኢራን ፕሬዚዳንት መግለጫ የተሰጡትም፥ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ያየር ላፒድ ኢራን በጭራሽ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንድትይዝ በማይፈቅደውና ከሞከረችም ሁሉንም የብሔራዊ ኃይላት ለመጠቀም ያስችላል የተባለ የቃልኪዳን ሰነድ መፈራረማቸውን ተከትሎ ነው።

ፕሬዚዳንት ባይደን በበኩላቸው በቀጠናው ኢራን-ሰራሽ ሰው- አልባ አውሮፕላኖች እንቅስቃሴ መጨመር ያስከተለውን ስጋት ያወገዙ ሲሆን፤ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነትም ተፈራርመዋል፡፡

ዋሽንግተን ቴህራን እንደዚህ ዓይነት ሰው- አልባ አውሮፕላኖችን ለሩሲያ ለመሸጥ ሙከራ አድርጋለች በማለት በተደጋጋሚ ስትወቅስ፥ ኢራን በበኩሏ ደጋግማ ማስተባበሏን አርቲ በዘገባው አስታውሷል።

አሜሪካ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማካይነት ከ2015ቱ የኒውክሌር ስምምነት ከወጣች በኋላ፥ ስምምነቱን እንደገና ለማደስ ቃል ቢገባም ፀረ-ኢራን ማዕቀብ ማንሳትን ያካተተ የዩራኒየም ማበልፀግን ለመገደብ አልተቻለም ያሉት ቃል አቀባዩ፥ ባይደን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ባደረጉት የመጀመሪያ ጉዞ በጉዳዩ ላይ ምንም የተሻሻለ ነገር አላሳዩም ብለዋል።

ባይደን ለባህረ ሰላጤው ለአሜሪካ አጋሮች ባስተላለፉት መልዕክት፥ ዋሽንግተን አካባቢውን ለመልቀቅ እቅድ እንደሌላት አረጋግጠዋል።

የባህረ ሰላጤው የትብብር ምክር ቤት ሀገራት እንዲሁም ግብፅ፣ ዮርዳኖስና ኢራቅም በጅዳ በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከእንግዲህ በቻይና፣ ሩሲያ ወይም ኢራን የሚሞላ ክፍተትን ትተን ርቀን አንሄድም ሲሉ ቃል ገብተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.