Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ዘለቄታዊ እድገት ላይ ያተኮረ ጉባኤ በባህርዳር እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል ዘለቄታዊ እድገት ላይ ያተኮረ የምሁራን ጉባኤ በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

ጉባኤው “የጋራ ራዕይና ግብ ለአማራ ህዝብ ዘለቄታዊ አንድነትና ሁለንተናዊ ስኬት” በሚል መሪ ቃል ነው እየተካሄደ ያለው።

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ የክልሉን እና የሃገሪቱን የወደፊት አቅጣጫ ከመወሠን አንፃር ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የምንገኝበት ጊዜ ነው ብለዋል።

እስካሁን ባለው ሂደት ውስብስብ ችግሮችን ማለፍ ቢቻልም ከፊት ለፊት ልንሻገራቸው የሚገቡ ፈተናዎች አሉብንም ነው ያሉት።

አያይዘውም እስካሁን በተጓዝንበት ጎዳና የተገኙ ስኬቶችን ስንቅ በማድረግ ተግዳሮቶችን መሻገርና ለአሸናፊነት መብቃት እንደሚገባም አውስተዋል።

ለዚህ ደግሞ የምሁራን ውይይት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው።

ኢትዮጵያ ጠንካራ፣ የተከበረችና የታፈረች ሀገር እንድትሆን የተረጋጋ ሠላም መፍጠርና ዴሞክራሲን መገንባት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

አቶ ደመቀ በንግግራቸው በጋራ አንድነት፣ አብሮነትና ሠላም ላይ መስራት እየተቻለ ሌሎች በሚፈጥሩት አጀንዳ መጠመድ እንደማይገባም አንስተዋል።

አመራሮች፣ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ የሚዲያ ተቋማት እና የማህበራዊ ትስስር ገጽ አንቂዎች ለህዝቡ ዘላቂ ጥቅም መረጋገጥ ከራሳቸው ዝና እና ክብር ተላቀው ችግር ፈቺ ስራዎችን መስራት እንደሚገባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የህዝቡን ዘላቂ ጥቅም ለማረጋገጥም በሁሉም ሚዛን ዜጎች ያለስጋት የሚኖሩባትና ለሁሉም የተመቸች ሀገርን ለመገንባት የአብሮነት ካባ በመላበስ መቆም እንደሚገባም ነው ያነሱት።

በጉባኤው ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የክልሉ ተወላጅ ምሁራን ተገኝተዋል።

ከዚህ ባለፈም በጉባኤው ላይ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊዎች ናቸው።

በሃገሪቱና በክልሉ ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታዎች እንዲሁም ባጋጠሙ ችግሮችና መልካም አጋጣሚዎች ላይ በመምከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ የጉባኤው አዓማ ነው ተብሏል።

ጉባኤው የክልሉ ምሁራን መማክርት ጉባኤን ጨምሮ በክልሉ ገዢና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ትብብር የተዘጋጀ ነው።

በናትናኤል ጥጋቡ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.