Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ደንበኞቹን የዘመናዊ ቆጣሪ ተጠቃሚ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት በክልሉ ለሚገኙ የከፍተኛ ኀይል ተጠቃሚ ደንበኞች የዘመናዊ ቆጣሪ (ስማርት ሜትር) ተጠቃሚ አደረገ፡፡

የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት በባሕር ዳር ከተማ ለሚገኙ የከፍተኛ ኀይል ተጠቃሚ ደንበኞች ነባር ቆጣሪዎችን በአዲሱ ቆጣሪ (በስማርት ሜትር) የመቀየር ሥራ መጀመሩን አስታውቋል።

በአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአውቶሜሽን ቴክኖሎጂና ኢነርጂ ማኔጅመንት ክፍል ስካዳ ኢንጂነር አሉበል ሞላ አዲሶቹ ቆጣሪዎች ከዚህ ቀደም የነበሩ የቆጣሪ ንባብ ክፍተቶችን የሚያሻሽሉና ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አዲሶቹ ቆጣሪዎች የቆጣሪ አንባቢ እንደማያስፈልጋቸው እና የደንበኞች ቅሬታን ሙሉ በሙሉ እንደሚቀርፍም ተገልጿል፡፡

የክልሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት 480 አዲስ ቆጣሪዎችን በመዘርጋት ሥራ የሚጀምር እንደሆነና በስድስት ከተሞች አገልግሎቱን እንደሚያዳርስ ተጠቁሟል።

የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት በባሕር ዳር፣ ደሴ፣ በወልድያ፣ በጎንደር፣ በደብረ ብርሃንና በደብረማርቆስ የሚገኙ ዲስትሪክቶች አዲሱን ቆጣሪ የመቀየር ተግባር እንደሚያከናውኑ ነው የተገለጸው።

በአማራ ክልል 7 ሺህ 200 ደንበኞች የአዲሱ ቆጣሪ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ መገለጹን አሚኮ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.