Fana: At a Speed of Life!

በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ 2ኛ ላይ ተቀምጣለች

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ ኦሬጎን እየተካሄደ በሚገኘው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ 2ኛ ስፍራን ይዛለች፡፡
 
በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ እስካሁን ሶስት የወርቅ እና ሶስት የብር ሜዳሊያ በማምጣት ነው ከአሜሪካ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው፡፡
 
በሴቶች 10 ሺህ ሜትር ለተሰንበት ግደይ የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ፣ በወንዶች ማራቶን ታምራት ቶላ ሁለተኛውን ወርቅ እንዲሁም በሴቶች ማራቶን ጎይተቶም ገብረስላሴ ሶስተኛውን ወርቅ ለሀገራቸው አስገኝተዋል፡፡
 
በተጨማሪም በወንዶች ማራቶን ሞስነት ገረመው ፣ በሴቶች 1 ሺህ 500 ሜትር ጉዳፍ ፀጋይ እና በወንዶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል ለሜቻ ግርማ እያንዳንዳቸው ለአገራቸው የብር ሜዳሊያ አስገኝተዋል፡፡
 
እስካሁን በተካሄደው ውድድር አሜሪካ በስድስት ወርቅ፣ በአራት ብር እና በ6 ነሐስ በውድድሩ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ መቀመጥ ችላለች፡፡
 
ኬንያ በበኩሏ በአንድ ወርቅ፣ በሶስት ብር እና በሁለት ነሐስ ከኢትዮጵያ በመቀጠል ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡
 
በሻምፒዮናው ከ192 አገራት የተወጣጡ 1 ሺህ 972 አትሌቶች በ50 የአትሌቲክስ ውድድሮች እየተሳተፉ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመላክታል።
 
በአሜሪካ ኦሬጎን እየተካሄደ የሚገኘው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የፊታችን ሐምሌ 17 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.