Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የ55 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አደረገች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ የ55 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አደረገች፡፡

ድጋፉ በዓለም አቀፉ የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት በኩል መደረጉም ነው የተገለጸው፡፡

የአሜሪካው ዓለምአቀፍ ተራድዖ ድርጅት ÷ ተጨማሪው የገንዘብ ድጋፍ ኢትዮጵያ ወቅታዊውን የምግብ አቅርቦት ችግር ለመቋቋም እና ወደፊት ከምግብ ጋር የተያያዙ አደጋዎችን ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት ተጨማሪ አቅም እንደሚገነባላት አስታውቋል፡፡

ፈንዱ የተገኘው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በፈረንጆቹ ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ በጀርመን በቡድን 7 የመሪዎች ጉባዔ ላይ ቃል በገቡት መሠረት የተፈጸመ ነውም ተብሏል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በጉባዔው አሜሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለምግብ ዕጥረት ቀውስ ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች 2 ነጥብ 76 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ መናገራቸው ተገልጿል፡፡

የአሜሪካው ተራድዖ ድርጅት የገንዘብ ድጋፉን ከሁለት ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ለምግብ እና ውሃ አቅርቦት ችግር ለተጋለጡ አርሶ እና አርብቶ አደሮችን እንዲሁም ቀሪ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለመደገፍ እንደሚያውለው አስታውቋል፡፡

የተራድዖ ድርጅቱ የገንዘብ ድጋፉን የውሃ አቅርቦት መሠረተ-ልማቶችን መልሶ ለመገንባት፣ ለግብርናው ዘርፍ የብድር አገልግሎት ለማቅረብ እንዲሁም የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ለማጠናከር እና ሥልጠና ለመሥጠት እንደሚያውለውም ተመልክቷል፡፡

የዘር እና የማዳበሪያ ማከፋፈያ ሥርዓት እንደሚዘረጋና አርሶ አደሮች አስፈላጊ የሚሏቸውን የእርሻ መሳሪያዎች እንዲገዙ እና የምግብ ምርት አቅርቦታቸውን እንዲያሳድጉ እንደሚያግዝም ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ተራድዖ ድርጅቱ ከ3 ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ የግብርና ቢዝነስ ተቋማት እና በድርቁ ለተጎዱ አርብቶ አደሮችን እና የማኅበረሰቦች ክፍሎችን ለማቋቋም ድጋፉን እንደሚጠቀምበትም አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም በፈንዱ ከ8 ሚሊየን በላይ ሰዎች የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ በሴፍቲ ኔት ኔት መርሃ ግብር ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚሰራም ተመልክቷል፡፡

የአርብቶ አደሮችን ሕይወት ለመቀየር፣ የብድር አገልግሎት ለማመቻቸት እና ለመሳሰሉት ተግባራት ፈንዱ ጥቅም ላይ እንደሚውልም ተብራርቷል፡፡

አሜሪካ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት ለማሻሻል በልማት እና በሰብዓዊ ሥራዎች 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ፈሰስ አድርጋለች ተብሏል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.