Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ መፈናቀልን ለመቀነስ ያስችላል የተባለለት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሠላም ሚኒስቴር ከዓለማቀፉ የሥደተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) እና ከደቡብ ኮሪያው የልማት ድርጅት (ኮይካ) ጋር በመሆን በኢትዮጵያ መፈናቀልን ለመቀነስ የሚያስችል ፕሮጀክት በይፋ ሥራ አስጀመሩ።

ፕሮጀክቱ በተፈጥሮ አደጋዎችና በግጭት በተጎዱ የሀገሪቱ ክፍሎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ሕይወት ለማሻሻልና መፈናቀልን በመቀነስ ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን የሚያስችል ነው ተብሏል።

በሠላም ሚኒስቴር ፌደራሊዝምና ግጭት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን፥ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ መፈናቀል መኖሩን አንስተው፥ መንግስት ለሰዎች ደኅንነት ቅድሚያ በመስጠት መፈናቀልን ለመቀነስ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ ገልፀዋል።

ሥደትና መፈናቀል በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ ያለ ችግር ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ፥ የኢትዮጵያ መንግስት የተፈጥሮ አደጋዎችና ሌሎች ችግሮችን መቋቋም የሚችል ማኅበረሰብ ለመገንባት ቁርጠኛ ነውም ብለዋል፡፡

ድርጅቶቹ ችግሩን ለመፍታት በጋራ ለመሥራት ላሳዩት ተነሳሽነት ምስጋና ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በቀጣይ ሦስት ዓመታት ፕሮጀክቱ አካታች የማኅበረሰብ ልማት ላይ የሚሠራ እና የተፈናቀሉ ዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ችግሮችንለ መፍታት፣ ብሎም ማኅበራዊ መረጋጋት ለመፍጠር እና የኅግ የበላይነትን ለማስፈንና ዘላቂ ሠላም ለመገንባት እንደሚሠራም ተገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.