Fana: At a Speed of Life!

አፍጋኒስታን 1 ሺህ 500 የታሊባን እስረኞችን ልትለቅ ነው

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 2 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍጋኒስታን 1 ሺህ 500 የታሊባን እስረኞችን ልትለቅ ነው።

የአፍጋኒስታኑ ፕሬዚዳንት አሽረፍ ጋኒ እስረኞችን ለመልቀቅ የተዘጋጀውን የትዕዛዝ ሰነድ ፈርመዋል።

በዚህ መሰረት የእርሳቸው አስተዳደር በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ 1 ሺህ 500 የታሊባን እስረኞችን የሚለቅ ይሆናል።

ከእስር የተለቀቁ የታሊባን ታጣቂዎች ደግሞ ዳግም ወደ ጦር ሜዳ እንዳይመለሱ የፅሁፍ ማረጋገጫ እንዲሰጡ የሚጠይቅ ስምምነትም ተካቶበታል።

ከዚህ በተጨማሪም ታጣቂ ሰርጎ ገቦች በአፍጋኒስታን እያደረሱት ያለውን ጥቃት እንዲያቆሙ የአሽረፍ ጋኒ አስተዳደር ጠይቋል።

ይህም ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ለመድረስ ለታሰበው የሰላም ስምምነት ተስፋ ሰጭ ነው ተብሎለታል።

ከእስረኞቹ መለቀቅ ጎን ለጎንም የአፍጋን ታሊባን የሰላም ድርድር ይካሄዳልም ነው የተባለው።

ይለቀቃሉ የተባሉት እስረኞች በመላ ሃገሪቱ በተለያየ ጊዜ የታሰሩ የታሊባን ታጣቂዎችን ስለማካተት አለማካተቱ ግን የተባለ ነገር የለም።

ረጅም ጊዜ ያስቆጠረው የአፍጋን ታሊባን የሰላም ድርድር በተለያዩ ምክንያቶች የታሰበውን ውጤት ማምጣት አልቻለም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በአሜሪካ አሸማጋይነት የተደረጉ የተናጠል ድርድሮች በሰነዶቹ ላይ ከቀረቡ የቃላት ትርጉምና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ እክል ገጥሟቸዋል።

አሜሪካ በበኩሏ ወታደሮቿን ከአፍጋኒስታን በተለያዩ ምዕራፎች ማስወጣት የሚያስችል ስምምነት ባለፈው ወር ከታሊባን ጋር መፈራረሟ ይታወሳል።

ከዚያን ጊዜ ወዲህም ቡድኑ የሚፈጽመውን ጥቃት እንዲያቆምና ለሰላም ድርድሩ ስኬታማነት የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርባለች።

ከትናንት ጀምሮም አሜሪካ በአፍጋን ከሚገኙ ወታደሮቿ የተወሰኑትን ማስወጣት ጀምራለች።

ምንጭ፦ ሬውተርስ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.