Fana: At a Speed of Life!

“የሙቀት ማዕበል” በአውሮፓ ደኖችን እያጋየ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በበርካታ የአውሮፓ ሀገራት የተከሰተው ከፍተኛ ሙቀት በቀሰቀሰው ሰደድ እሳት ከፍተኛ ውድመት እያስከተለ መሆኑ ተገለጸ።

በቀዝቃዛ የዓየር ንብረቷ የምትታወቀው ብሪታኒያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ የሆነ የሙቀት መጠን አስመዝግባለች።

በጀርመንም ከፍተኛ የሙቀት መጠን የተመዘገበ ሲሆን፥ በፖርቹጋል ከሙቀቱ ጋር በተያያዘ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።

በፈረንሣይም በ64 የተለያዩ አካባቢዎቿ ከፍተኛ የሙቀት መጠን መዝግባለች ነው የተባለው፡፡

በፈረንሳይ ደቡብ ምዕራብ ክፍል ከ30 ዓመታት ወዲህ ሀገሪቷ አይታ የማታውቀውን ከፍተኛ የሰደድ እሳት የተከሰተ ሲሆን፥ ከፈረንጆቹ ሐምሌ 12 ጀምሮ በጊሮንዴ ግዛት የሚገኘው ከ20 ሺህ 300 በላይ ሄክታር የወይን ማሳ በእሳት መውደሙም ነው የተገለጸው፡፡

በእሳት አደጋው ወደ 37 ሺህ የሚጠጉ ፈረንሳያውያን ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የፈረንሳይ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

አሁን ላይ በአውሮፓ ደኖች ላይ የተቀሰቀሰው የሰደድ እሳት ተባብሶ ቀጥሏልም ነው የተባለው፡፡

የዓለም የሚቲዮሮሎጂ ድርጅት ኃላፊ ፔቴሪ ታላስ ÷ “ከዚህ በኋላ የሙቀት ማዕበል በአውሮፓ አኅጉር የሚለመድ ይሆናል ፤ ከዚህ የባሰም ገና ይመጣል” ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

የብሪታኒያ የእሳት አደጋ መከላከያ ሠራተኞች ከባድ የእሳት አደጋዎች በቀጣይ ሊኖር ይችላል በሚል በተጠንቀቅ ይገኛሉ ነው የተባለው።

በለንደን ምሥራቃዊ ክፍል በምትገኘው ዌኒንግተን ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ መኖሪያ ቤቶችን እያነደደ ሲሆን ከቁጥጥር ወጥቶ በርካታ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውም ነው የተነገረው፡፡

የሙቀት ማዕበሉ በቤልጂዬም፣ ኔዘርላንድስ፣ ግሪክ፣ ስፔን እና ጣልያንን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት የተመዘገበ ሲሆን፥ ከዚህ ጋር በተያያዘም በርካቶች ለህልፈት ተዳርገዋል ነው የተባለው።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.