Fana: At a Speed of Life!

በአፋር “ዳርሳ ጊታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” መልሶ ግንባታ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል ካሳ ጊታ የሚገኘውን “ዳርሳ ጊታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” መልሶ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።

የመሰረት ድንጋዩን ያስቀመጡት የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ናቸው።

የዳርሳ ጊታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በጦርነቱ ወቅት በአሸባሪው ህወሓት በመውደሙ የመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ጫና ደርሶበት ቆይቷል፡፡

የኅንጻው መገንባት በውድመቱ ትምህርታቸውን አቋርጠው የነበሩትን 40 ተማሪዎች መመለስ እንደሚያስችል እና ተማሪዎች ምቹ ክፍሎች ውስጥ በተሻለ ሁኔታ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ÷ ግንባታው በታቀደለት ጊዜ እንዲጠናቀቅና ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉ ያስታወቁ ሲሆን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ደግሞ በግጭት የፈረሱ ትምህርት ቤቶች በአዲስ መልክ ምቹ ሆነው እንዲገነቡ ፕሮጀክት ቀርጸው እየሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል።

የትምህርት ቤቱን ግንባታ በ9 ወር ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱም ነው የተነገረው።

በክልሉ 65 ትምህርት ቤቶች በጦርነቱ ሙሉ በሙሉ የወደሙ ሲሆን ፥ ሁሉም ደረጃቸውን በጠበቁ መልኩ ይገነባሉ ተብሏል።

የትምህርት ቤቱ ግንባታ ትምህርት ሚኒስቴር ያዘጋጀው የ”አዲሲቷ ኢትዮጵያ አዲስ ትምህርት ቤቶች” ፕሮጀክት አካል ሲሆን ሙሉ ወጪውም በ”ኢትዮጵያ ትረስት ፈንድ” ይሸፈናል ነው የተባለው፡፡

በመርሐ ግብሩ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ችግኝ ተክለዋል።

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.