Fana: At a Speed of Life!

በቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል ከ83 ሺህ በላይ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል- የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ83 ሺህ በላይ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ታረቀኝ ታሲሳ እንደገለጹት÷ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በሰው ሠራሽና በተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ከ442 ሺህ በላይ ዜጎች አሉ፡፡
ለእነዚህ ዜጎች መንግስት ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር ሰብዓዊ ድጋፎች ለማድረስ ጥረት እያደረገ መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
በክልሉ የጸጥታ ችግር የነበረባቸውን አካባቢዎች ወደ ዘላቂ ሰላም ለመመለስ ሲሠራ መቆየቱን ጠቁመው÷ በተሠሩት ሥራዎችም አንዳንድ አካባቢዎች ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡
ዘላቂ ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ነባር ቀያቸው የመመለስና መልሶ የማቋቋም ስራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጸው÷ እስካሁን ከ83 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን አስረድተዋል፡፡
ወደቀያቸው ለተመለሱ ዜጎችም መንግስት የተለያዩ ሰብዓዊ ድጋፎችን ጨምሮ የእርሻ ትራክተር፣ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን እየተሠሩ ያሉ የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመው ለውጤታማነቱም ባለድርሻ አካላት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.