Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስቴሩ በጦርነቱ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማ በጦርነት ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች የ8 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የአልባሳትና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጀን በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንዳሉት ፥ ሚኒስቴሩ በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ ከተሞችን መልሶ ለማቋቋም እየሰራ ነው ፡፡

ለከፋ ችግር ለተጋለጡ ወገኖችም የሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው÷በዚህም አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት በሰቆጣ ከተማ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች 8 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የሰብዓዊ ድጋፍ መቅረቡን ገልፀዋል።

ሚኒስቴሩ በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች ከሚያደርገው የሰብዓዊ ድጋፍ ባሻገር ለሰቆጣ ከተማ ዘላቂ ልማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲሚቀጥል አቶ ፈንታ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳዳሪ አቶ ስቡህ ገበያው÷ ተቋሙ ዛሬ ያደረገው ድጋፍ የተፈናቀሉ ተማሪዎች በቀጣይ የትምህርት ዘመን በትምህርት ቁሳቁስ ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይሆኑ ትልቅ ሚና እንዳለውም አመልክተዋል።

የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ መላሽ ወርቃለማው በበኩላቸው ፥ የተደረገውን ድጋፍ በቀጥታ ለተረጂዎች በአግባቡ እንደሚደርስ አረጋግጠዋል።

ሚኒስቴሩ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ከተሞች ለሚያደርገው የመልሶ ግንባታ በሰቆጣ ከተማ በአንድ ትምህርት ቤት ስምንት ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችና አንድ የሳይንስ ቤተሙከራ ግንባታ እያከናወነ መሆኑን ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.