Fana: At a Speed of Life!

የፌደራል ፖሊስ እና የጣሊያን ፖሊስ በሁለትዮሽና በዓለም አቀፍ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የጣሊያን ፖሊስ በሁለትዮሽና በዓለም አቀፍ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ በሮም ውይይት አደረጉ።

በፌደራል ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የተመራው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የልዑካን ቡድን ወደ ጣሊያን ሮም ተጉዞ ከጣሊያን ፖሊስ ተቋም ኃላፊ ኮማንደር ጀነራል ቴኦ ሉዚ ጋር በመወያየት ፖሊስን ለማዘመን በሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችና በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በትብብር አብሮ ለመስራት ተስማምተዋል።

ልዑካን ቡድኑ ሮም ሲገባ በጣሊያን ፖሊስ ደማቅ አቀባበል የተደረገለት ሲሆን ፥ ኮሚሽነር ጄነራሉም ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበልና የጣሊያን መንግስት እያደረገ ስላለው ድጋፍ እና ትብብር አመስግነዋል።

በውይይቱ ወቅት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በአፍሪካ ካሉ ምርጥ አምስት ፖሊስ ተቋማት ተርታ ለመሰለፍ ራዕይ ሰንቆ በከፍተኛ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ኮሚሽነር ጄነራሉ ለጣሊያን ፖሊስ ኮማንደር ጀነራል ገልፀው ፥ አሁን የደረሰበትን የእድገት ደረጃም አብራርተዋል።

በሪፎርም በተሰሩ ስራዎች ወንጀልን በቴክኖሎጂ ታግዞ ለመከላከልና ለመመርመር የሚያስችሉ የፎረንሲክ ምርመራ ላብራቶሪ አደራጅቶ እየሰራ መሆኑንና የተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መታጠቁንም አንስተዋል።

በአዲሱ መዋቅራዊ አደረጃጀት የቱሪዝም፣ የአቪዬሽን፣ የምድር ባቡር፣ የዩኒቨርሲቲ፣ ፈጥኖ ደራሽ እና የኢንዱስትሪ ፖሊስ ማደራጀቱንም አስረድተዋል ።

ተቋሙ በአፍሪካ ቀንድ ‘ሮክ’ ከተባለ ድርጅት ጋር ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በተለይም ህገ ወጥ የሰዎችና የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል ውጤታማ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡

ኮማንደር ጀነራል ቴኦ ሉዚ በበኩላቸው ፥ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ለብዙ ዘመናት የቆየ መሆኑን ተናግረው ፥ ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ሁለቱ የፖሊስ ተቋማት በትብብር መስራት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፈደራል ፖሊስ ወጣት የፖሊስ መኮንን አመራሮችን አቅም ለማሳደግ እንዲቻል በጣሊያን ፖሊስ አካዳሚ ገብተው በቴክኖሎጂ፣ በፎረንሲክ ምርመራና በፖሊስ ኮማንዶ ሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና መውሰድ እንደሚችሉም አረጋግጠዋል፡፡

ተቋሙ የጀመረው ሪፎርም ውጤታማ መሆኑን ገልፀው ÷በቀጣይም ሂደቱንና አፈፃፀሙን የሚያማክሩ የጣሊያን ፖሊስ አማካሪዎችን መድበው ለውጡን የበለጠ ለማገዝ ቃል መግባታቸው ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተጀመረውን የፎረንሲክ እንዲሁም የዲኤንኤ ምርመራ አቅሞችን ለማሳደግ የተለያዩ ቴክኖሎጂ እና የሰው ኃይል ስልጠና ድጋፎች ይሰጣሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ልዑኳን ቡድን የጣሊያን ፖሊስ ኮማንድ ኮንትሮል ሴንተር፣ የፎረንሲክና የዲኤንኤ ላብራቶሪን ተዘዋውሮ በመጎብኘት የልምድ ልውውጥ ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን ፥ የሁለቱ የፖሊስ ተቋማት የጋራ ስጋቶች የሆኑትን ሽብርተኝነትና ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ተባብረው ለመከላከል ተስማምተዋል፡፡

ኮማንደር ጀነራል ቴኦ ሉዚ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አዘጋጅነት በጥቅምት 2015 ዓ.ም በሚካሄደው የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ ኮሚሽነሮች ህብረት ስብሰባ ላይ እንደሚገኙ ቃል መግባታቸውም ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.