Fana: At a Speed of Life!

በ2014 በጀት ዓመት ለጂቡቲ እና ሱዳን ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከ95 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመት ለጂቡቲና ሱዳን ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከ95 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን÷ ተቋሙ በጅምላ የኤሌክትሪክ ሽያጭ ለሀገር ውስጥና ለውጭ አገራት ደንበኞች እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።
በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመትም ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ለከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች፣ እንዲሁም ለሱዳንና ጂቡቲ ኃይል በሽያጭ በማቅረብ ገቢ መሰብሰብ እንደቻለ ተናግረዋል።
በዚህም ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 9 ሺህ 472 ጊጋ ዋት ማቅረቡን ገልፀው÷ለከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች የእቅዱን 90 በመቶ እንዲሁም ለኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር የእቅዱን 116 በመቶ ኃይል ማቅረብ መቻሉን አስረድተዋል።
ተቋሙ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለጂቡቲ 527 ጊጋ ዋት ኃይል ለማቅረብ አቅዶ 611 ጊጋ ዋት ማቅረብ መቻሉን እና ለሱዳን ደግሞ 1 ሺህ 93 ጊጋ ዋት በሰዓት ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት 12 ሺህ 30 ጊጋ ዋት ኃይል አቅርቧል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፡፡
ተቋሙ ለጂቡቲና ሱዳን ካቀረበው የኃይል ሽያጭ 95 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ እንዳገኘ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ካቀረበው ኃይል 11 ቢሊየን ብር እንዲሁም ከኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር ደግሞ 364 ሚሊየን ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.