Fana: At a Speed of Life!

የኢጋድ አባል ሀገራት ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን መቋቋም የሚያስችል እቅድ ሊተገብሩ ይገባል- ዶ/ር ወርቅነህ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አባል ሀገራት ወቅታዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን መቋቋም የሚያስችል እቅድ ሊተገብሩ እንደሚገባ የኢጋድ ዋና ፀሃፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ አስገነዘቡ።

የኢጋድ 14ኛው የአስተባባሪ ኮሚቴ ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

ስብሰባው በመጪው ዓርብ የድርቅ አደጋን መቋቋምና በዘላቂነት መከላከል ላይ ትኩረቱን አድርጎ በአዲስ አበባ የሚካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ አካል ነው ተብሏል።

በጉባኤው የሁሉም የኢጋድ አባል ሀገራት ድርቅን ለመቋቋምና በዘላቂነት ለመከላከል እያከናወኑት ያለው የእቅድ ትግበራ ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግበት ተገልጿል፡፡

በጉባኤው መክፈቻ የተገኙት የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ÷ኢጋድ በቀጠናው ያሉ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ድርቅን የመቋቋም አቅማቸውን ለማጠናከር ሲሰራ መቆየቱን አውስተዋል።

በቀጠናው ባለፉት አራት አስርት ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ መከሰቱን የገለፁት ዋና ጸኃፊው÷ በዚህም በቀጠናው የምግብ ዋስትና የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በቀጣናው 50 ሚሊየን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች የምግብ ዋስትና እንደሚያስፈልጋቸውም ነው የተናገሩት፡፡

በመሆኑም የቀጣናው አገራት በዓለም ላይ እየተከሰቱ ያሉ ተለዋዋጭ ተፅእኖዎችን መቋቋም የሚያስችሉ እቅዶችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ በበኩላቸው÷ በቀጣናው የተከሰተው ተደጋጋሚ ድርቅ፣ ጎርፍ እና ሌሎች ከአየር ንብረት ጋር የተገናኙ አደጋዎች በማህበረሰቡ ኑሮ ላይ ተጽእኖ መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ችግሩን መቋቋም የሚያስችል የአቅም ግንባታ ፕሮጀክቶችን ቀርጻ ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኗን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.