Fana: At a Speed of Life!

ለኬንያውያን የሰርክ ምግብ ማዘጋጃነት የሚውለው የበቆሎ ዱቄት ዋጋ በግማሽ መቀነሱ ተነገረ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኬንያ በዋና ምግብነት የሚያገለግለው የበቆሎ ዱቄት ዋጋ በግማሽ መቀነሱ ተነገረ፡፡

የሀገሪቷ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እርምጃውን የወሰዱት የሀገሪቷ መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ተከትሎ የኑሮ ውድነቱን ኬንያውያን እንዲቋቋሙት ለማስቻል ነው ተብሏል።

ኬንያታ አዲሱን የዋጋ ማሻሻያ ያወጡት መንግስታቸው ከሀገሪቷ የበቆሎ አቀነባባሪ ፋብሪካዎች ጋር ለቀናት ድርድር ካካሄደ በኋላ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኡሁሩ ኬንያታ በሀገር ውስጥ ለተከሰተው የኑሮ ውድነት መባባስ የሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት፥ በዓለም አቀፉ የነዳጅ እና የምግብ ዋጋ ላይ ተጽዕኖ በማሳደሩ መሆኑን በዋና ምክንያትነት ይጠቅሳሉ፡፡

በሌላ በኩል የኬንያ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ፕሬዚዳንቱ ሦስት ሣምንታት ከሚቀረው የ2022 ሀገራዊ ምርጫ በፊት በበቆሎ ዱቄት ላይ የዋጋ ማስተካከያ ያደረጉት ደጋፊዎቻቸውን ለማበራከት እና ምርጫውን ለማሸነፍ ነው ይላሉ፡፡

የኬንያ ስታቲስቲክስ ቢሮ ÷ የሀገሪቷ ጠቅላላ ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት መጠን 7 ነጥብ 9 በመቶ መድረሱን አስታውቋል።

በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ የተከሰተው ግሽበት ደግሞ 13 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱንም ነው የገለጸው።

በአሁኑ ወቅት የኬንውያን አንገብጋቢ ጥያቄ የመሠረታዊ ሸቀጦች በተለይም የሰርክ ምግባቸው የሆነውን “ኡጋሊ” ለማዘጋጀት በዋናነት የሚጠቀሙት የበቆሎ ዱቄት ላይ የዋጋ ማስተካከያ እንዲደረግ መሆኑን ሲ ጂ ቲ ኤን እና ቢ ቢ ሲ ዘግበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.