Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት እየተሠራ ያለው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ከንቲባው ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት እየተሠራ ያለው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ ተናገሩ፡፡
አቶ ጃንጥራር ዓባይ ከአዲስ አበባ ከተማ ገበያ ማረጋጋትና ኑሮ ውድነት ማሻሻያ ግብረ ኃይል ኮሚቴ ጋር የ15 ቀን ሪፖርት ገምግመዋል፡፡
በግምገማው ላይ÷ ባለፉት 15 ቀናት ያለውን የኑሮ ውድነት ለማሻሻል የሸገር ዳቦ አቅርቦትን እና የእሁድ ገበያን ከማስፋፋት አንጻር እንዲሁም የዘይትና የስኳር አቅርቦት የተሻለ እንደነበር ተገልጿል፡፡
በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በጤፍ ዋጋ ላይ ከመደበኛው ዋጋ በቅናሽ ማቅረብ እንደተቻለም ተመላክቷል፡፡
የማህበራትን አቅም ከማጠናከር አንጻር ዝቅተኛ የሆኑ ማህበራትን በማዋሃድ አቅማቸውን የማጠናከር ሥራ መሠራቱም በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡
ሕገ ወጥነትን ለመከላከል በተለያዩ ተቋማት ላይ ክትትል በማድረግ ከ1 ሺህ 600 በላይ ሕገ ወጥ ተቋማትን በመለየት ከ1 ሺህ 300 በላይ የሚሆኑትን ወደ ሕጋዊነት ማስመለስ መቻሉን የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
አቶ ጃንጥራር ዓባይ በግምገማው ላይ እንደገለጹት÷ በቀጣይ ያለውን የኑሮ ውድነት ጫና ለመቀነስ የማህበራትን ሪፎርም ከአገልግሎት አሰጣጥ፣ የባከነ ንብረት ከማስመለስ እንዲሁም የምርት አቅርቦትን ከማሳለጥ አንጻር በአግባቡ ሊሠራ ይገባል፡፡
የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የተመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ኦዲት ተደርጎ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.