Fana: At a Speed of Life!

የመዲናዋን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት የሚፈታ ፕሮጀክት ጥናትና ዲዛይን ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት እንደሚፈታ የታመነበት ፕሮጀክት ጥናት እና ዲዛይን መጠናቀቁን የከተማዋ ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

ከፋና ብሮድካስቲን ግኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዘሪሁን አባተ÷ ፕሮጀክቱ አንድ ቢሊየን ዶላር ወጪ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ 6 ዓመት እንደሚፈጅም ነው የተናገሩት።

የፕሮጀክቱ ጥናት እና ዲዛይን መጠናቀቁን የገለጹት ኢንጂነር ዘሪሁን፥ ባለስልጣኑ የገንዘብ ማፈላለግ ስራም ጀምሯል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን ግን የከተማ አስተዳደሩን ጨምሮ የፌዴራል ተቋማትም ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸው ነው ዋና ስራ አስኪያጁ ያሳሰቡት።

ባለስልጣኑም በአስቸኳይ የመዲናዋን የመጠጥ ውሃ ችግር የሚያቃልሉ ስራዎችን እየሰራ ነው ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ፥ በ2015 በጀት ዓመት በቀን 75 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ ማምረት የሚችል ፕሮጀክት እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡

ኢንጂነር ዘሪሁን እንዳሉት፥ የመዲናዋ የውሃ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እይጨመረ ሲሆን÷ በአጭር ጊዜ ሊጠናቀቁ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት መስራት ችግሩ እንዳይባባስ ያግዛል።

እንዲሁም ከፌዴራል ተቋማት ጋር የሚሰሩ ግድቦችን የማፋጠን ስራ መስራት አንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡

የአዲስ አበባ የውሃ ፍላጎት በዚህ ዓመት ብቻ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ሲሆን÷ የባለስልጣኑ ውሃ የማምረት አቅም ግን 644 ሺህ ሜትር ኪዩብ ብቻ ነው ብለዋል።

በዙፋን ካሳሁን

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.