Fana: At a Speed of Life!

ለፌደራል መሬት ይዞታዎች ካርታ ማዘጋጀት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እና የመሬት ልማት ባንክ ኮርፖሬሽን የፌደራል መሬት ይዞታዎችን ካርታ በጋራ ማዘጋጀት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቱሉ በሻህ እና የመሬት ልማት ባንክ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ሌንሳ መኮንን ተፈራርመውታል።

በስምምነቱ መሰረት የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በሳተላይት የተደገፈ ምስል እና የአየር ላይ ፎቶዎችን በማንሳት ይዞታዎቹን የመለየት ስራ የሚሰራ ሲሆን፥ የመሬት ልማት ባንክ ኮርፖሬሽን ደግሞ መረጃዎችን በማጠናቀር ለሚፈለገው አላማ እንዲውሉ የማድረግ ስራ ይሰራል።

በሂደቱ የመሬት መረጃዎችን መሰብሰብ፣ በምን ያክል ልኬትና ቦታ እንደሚገኙ መለየት፣ ለምን ግልጋሎት እንደዋሉና ያልዋሉትንም የመለየት ስራ ይሰራል።

ከዚህ ባለፈም በመሬቱ ላይ ያሉ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሃብቶችን መለየት፣ ለመስኖ ስራ፣ ለግድብ እና ለሌሎች ግልጋሎቶች መዋል አለመዋላቸውን መለየትና ለልማት ዝግጁ ማድረግም ሌላኛው የስራው አካል ነው ተብሏል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር አብርሃም በላይ የመሬት ካርታ ዝግጅት ስራው ውድ የሆነውን የመሬት ሃብት በቴክኖሎጂ በመለየት ከብክነት በፀዳ መልኩ ጥቅም ላይ ለማዋል ያስችላል ብለዋል።

የፌደራል መሬት ይዞታዎች ካርታ ዝግጅት ስራው በአዲስ አበባ የሚጀመር ሲሆን ከ4 እስከ 6 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞለታል።

የአየር ካርታ የማንሳት ስራው በ30 ሴንቲ ሜትር ርቀት ውስጥ ያለን ምስል መለየት በሚያስችል የምስል ጥራት የሚሰራ መሆኑን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

https://www.facebook.com/fanabroadcasting/
 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.