Fana: At a Speed of Life!

የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ጀማሪ ኦፊሰሮችን አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሥር የሚገኘው የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በዛሬው ዕለት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ጀማሪ ኦፊሰሮችን አስመርቋል፡፡

በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ኮሚሽነር እንዳሻው ጣሰው ÷ ተመራቂዎች ኅብረተሰቡን በቅንነት ፣ በትህትናና በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሩህተስፋ ሙሉጌታ በበኩላቸው ÷ ዜጎች የሚገባቸውን አገልግሎት በበቂ ሁኔታ ፣ ጥራት እና ፍጥነት የማግኘት መብታቸውን ለማረጋገጥ ተመራቂዎቹ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው አስምረውበታዋል፡፡

ባለሙያዎቹ ሀገራዊ ጥቅምና ደኅንነትን ባስጠበቀ እና ሥነ -ምግባር በተሞላበት ሁኔታ እንዲያገለግሉም ነው አቶ ብሩህተስፋ ያሳሰቡት፡፡

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አሁን የጀመረው የሰው ኃይል ሥልጠና የሪፎርሙ ትግበራ አካል መሆኑንም የገለጹ ሲሆን፥ በቀጣይ አገልግሎቱን ለኅብረተሰቡ በጥራትና በተዓማኒነት ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን ካሳ በበኩላቸው ÷ ዩኒቨርስቲ ኮሌጁ ለኢሚግሬሽን ጀማሪ ኦፊሰሮች የሥራ ስምሪት የሚሆን ጠቃሚና ውጤታማ የሆኑ ሥልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል ብለዋል።

አቶ ወንድወሰን ÷ ዩኒቨርስቲ ኮሌጁ ቀደም ሲል አጫጭር ሥልጠናዎች እንዲሁም በዲፕሎማና በዲግሪ ደረጃ ትምህርት ይሰጥ እንደነበረ ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ለሀገር ውስጥ ባለድርሻ አካላትና ለውጭ አቻ የመረጃና ደኅንነት ተቋማት የመረጃ ኪነ ሙያ ሥልጠና እየሠጠ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

በአሁኑ ወቅትም አቅሙን በማሳደግ በ2015 ዓ.ም ተማሪዎችን ተቀብሎ በኢንተለጀንስ ፣በደኅንነትና በሳይበር ሴኩሪቲ የጥናት ዘርፎች በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች ለማሠልጠን ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.