Fana: At a Speed of Life!

ስዊዘርላንድ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነቷን ማጠናከር እንደምትፈልግ ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ ከስዊዘርላንድ አምባሳደር ታማራ ሞና ጋር መከሩ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያና በስዊዘርላንድ መካከል ያለውን የቆየና ታሪካዊ ግንኙነት በምክክራቸው ወቅት አድንቀዋል።

ሁለቱ ሀገራት መደበኛ የፖለቲካ ምክክርና የተለያዩ የንግድና ኢንቨስትመንት ስራዎችን በመጀመር ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ያላቸውን አቅም መፈተሽ አለባቸውም ብለዋል አቶ ደመቀ።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታና መንግስት እስካሁን እያከናወናቸው ስላላቸው የሰላም ግንባታ ስራዎች ለስዊዘርላንድ አምባሳደር አብራርተዋል።

በፈረንጆቹ 2023/24 የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ለሆነችው ስዊዘርላንድ እንኳን ደስ አላችሁ ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፥ ሀገሪቱ እንደተለመደው በዓለምአቀፍ አጀንዳዎች ላይ ሚዛናዊና ምክንያታዊ አቋም ትይዛለች የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የስዊዘርላንድ አምባሳደር በበኩላቸው ፥ ሀገራቸው በምክር ቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተለዋጭ አባል ስትሆን እንደ ዘላቂ ሰላም፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የመንግስታቱን ድርጅት ውጤታማ ለማድረግና ለዜጎችን መብት መከበር ቅድሚያ እንደምትሰጥ ገልጸዋል።

አምባሳደሯ አክለውም ፥ ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ ቋሚ አባልነት ለበርካታ ጊዜያት ያገለገለች ሀገር በመሆኗ ልምዷን ለስዊዘርላንድ እንድታካፍል መጠየቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በርካታ የስዊዘርላንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው የገለጹት አምባሳደር ታማራ ሞና ፥ ስዊዘርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በተለይም በንግድ እና ኢንቨስትመንት ላይ የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.