Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ ከኦሮሚያ ክልል ከተውጣጡ አባ ገዳዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ እና የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከአባ ገዳዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር ተወያዩ።

በሀገሪቱ እንዲሁም በኦሮሚያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት ትናንት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በስብሰባው ላይም ከሁሉም የኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ አባ ገዳዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሴቶች እና ወጣቶች ተወካዮች ጋር ተሳትፈዋል።

የስብሰባው ተሳታፊዎችም በወቅታዊ የሀገሪቱ ጉዳዮች እና የህዝቡን አንድነት በማስመልከት ያሏቸውን ጥያቄዎች እና ሀሳቦች አንስተው ውይይት ተደርጎበታል።

ተሳታፊዎቹ ሀሰተኛ መረጃን የሚያሰራጩ በእኛ ውስጥ ቦታ የላቸውም፣ ለሀገሪቱ የሚቆረቆር ሰው ካለ ስለ ሀገሪቱ ብቻ ይናገር፣ መንግስትም የህግ የበላይነትን ማስጠበቅ አለበት፤ ችግሮቻችንን ባለን ባህል እና እሴት መሰረት በመፍታት አንድነታችንን ማጠናከር አለብን የሚሉ ሀሳቦች ከተሳታፊዎች ተነስተዋል።

ህዝቡን ማደናገር መቆም አለበት፣ መገናኛ ብዙሃን በህግ አግባብ ስራቸውን መስራት አለባቸው፤ ረጅም መጓዝ ስለምንፈልግ በአንድነት ሆናችሁ ህዝቡን አስተባብሩ የሚሉትም ሌሎቹ ከተሳታፊዎች የተነሱ አስተያየቶች ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሰጡት ምላሽና አስተያየትም፥ እኛ የኦሮም ህዝብ ጥያቄ እና የፌዴራል ስርዓትን ወደኋላ ለመመለስ አንሰራም፤ ከእኛ የሚነሳ ሀሳብ የማይስማማው ካለ ሌላ አማራጭ ሀሳብ ማቅረብ ነው ያለበት ብለዋል።

እርስ በእርስ በመገዳደል እና በመጎዳዳት መሻገር አይቻልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ መንግስት የፌደራሊል ስርዓትን ወደኋላ የሚመልስ ምንም አይነት ስራ እየሰራ እንዳልሆነም አብራርተዋል።

የሀገር ሽማግሌዎች እና እና አባ ገዳዎች ያኮረፉ አካላትን እንዲያናግሩ እንዲሁም መንግስት ከህዝቡ ሀሳብ እና ፍላጎት ውጭ ከወጣ ያኔ ውሳኔ አሳልፉ ሲሉም ተናግረዋል።

“ይህንን መንግስት በሁለት ቀን እንበትናለን የሚሉ አካላት እንደዚህ አይነት አቅም ካለቸው፤ ለምን ባለፉት ዓመታት ህዝብ ሲሰቃይ ሀገር ጥለው ሸሹ፤ ለምንስ እነሱ ሄደው የኦሮሞ ህዝብ ሲቸገር ከረመ፤ ወይስ ኦሮሞ ሀገር መምራት ሲጀምር ነው ነገር የቀለለላቸው” ያሉት ዶክተር አብይ፥ “እንዲህ አይነት ነገር አይጠቅምም፤ አንዱ አንዱን መናቅ ትክክል አይደለም” ብለዋል።

ልዩነቶቻችንን በውይይት በመፍታት የህዝቡ እንድነት እንዲጠናከር መስራት ይጠበቅብናል ማለታቸውን የኦቢኤን ዘገባ ያመለክታል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፥ ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር እንዲረጋጋ ያደረጉትን አካላት አመስግነዋል።

እንዴት ከችግር ውስጥ እንደወጣን እናውቃለን ያሉት አቶ ሽመልስ፥ ይህንን መንገድ በማጠናከር፣ ብሄር ብሄረሰቦችን አቅፎ በመያዝ እና የሀይማኖት እኩልነትን በማረጋገጥ ያለምንም ግርግር የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው፥ ትናንት እዚህ ልንደርስ የቻልነው በመደማመጥ፣ በመደጋገፍና በአንድነት በመቆም ነው ብለዋል።

እዚህ ቦታ የተደረሰው ከፍተኛ መሰዋእትነት በመክፈል ነው ያሉት አቶ ለማ፥ እዚህ የደረሰውን ትግል ማሻገር የሁሉም ተሳትፎ ይጠይቃል፤ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ወደኋላ አይመለስም፤ ለዚህም ስጋት አይግባችሁ ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.