Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ምክር ቤት በሀዋሳ ከተማ ሲያካሂድ የቆየው መደበኛ ጉባኤ ልዩ ልዩ ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቀቀ።

በምክር ቤቱ የተሾሙት ሁለት አስፈጻሚ አካላትና 98 በተለያየ ፍርድ ቤት ደረጃ የሚሰሩ ዳኞች ናቸው።

ከክልሉ ስራ አስፈጻሚ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች በተጓደሉት ሁለት የካቢኔ አባላት ምትክ በርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ ለቀረቡ አባላት ሹመት የተሰጠ መሆኑም ተመልክቷል።

በዚህም መሰረት ምክር ቤቱ፥ አቶ ዳንኤል ዳምጠውን የደቡብ ክልል ደንና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ሎሬ ከኩታ ደግሞ የአርብቶ አደር ጉዳዮች ልማት ቢሮ ኃላፊ አድርጎ በአብላጫ ድምጽ ሹመታቸውን አጽድቋል።

ምክር ቤቱ በተጨማሪም ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ለከፍተኛ፣ ለወረዳና ለከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች የቀረቡ የ98 እጩ ዳኞችን ሹመት ነው ያፀደቀው።

የዳኞችን ሹመት ለምክር ቤት ያቀረቡት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሲኖ አቡሬ፥ ዳኞቹ በአሰራሩ መሰረት በተለያዩ መስፈርቶች የተመለመሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የዳኞቹ ሹመትም የፍርድ ቤቶችን አሰራር ቀልጣፋ ለማድረግና የአገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

ተሿሚዎቹም በምክር ቤተ ፊት ቀርበው ቃለ መሐላ ፈጽመዋል።

ምክር ቤቱ ለሦስት ቀናት ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ አጽድቋል።

ዛሬ በመጨረሻ ቀን ውሎው የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ሪፖርትና ቀጣይ እቅድ ላይ ተወያይቶ ካጸደቀ በኋላ ጉባኤውን አጠናቋል።
ምክር ቤቱ የክልሉን የ2015 በጀት ዓመት ከ46 ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ብር በላይ ትናንት ማጽደቁ ይታወሳል።

በቢቂላ ቱፋና ኢዜአ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.