Fana: At a Speed of Life!

አረንጓዴ ዐሻራ የአንድነት እና የአብሮነት ማሳያ መሆኑን የመዲናዋ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአንድነት እና የአብሮነት ማሳያ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከከተማዋ የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር የፋይናንስ ድጋፍ በጉለሌ የዕጽዋት ማዕከል የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡

የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሀፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ በመርሐ ግብሩ ወቅት ባሰሙት ንግግር÷ በዘንድሮው አመት ጉባኤው 500 ሺህ ችግኞችን ለመትከል ማቀዱን ጠቅሰው በዛሬው እለት የተከናወነው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርም የዕቅዱ አካል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህንን ችግኝ ስንተክል ከልዩነት ይልቅ ወንድማማችነትን፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፣ መከባበርንና አብሮነትን ልናጎለብት ይገባልም ነው ያሉት፡፡

የአዲስ አበባና የጉራጌ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና አዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በበኩላቸው÷” ችግኝ መትከል የተቀደሰ ተግባር ነው፤ ፈጣሪ ካዘዘን ተግባራት በጎ ሥራ መስራት አንዱ ነው፤ ጉባኤያችን ከሰላም እሴት ግንባታ በተጨማሪ ማህበራዊ ስራዎችን የአቅመ ደካሞች የቤት እድሳት እና ችግኝ ሲተክል ቆይቷል”ሲሉ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት ፕሬዚዳንት እና የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ሼኽ ሱልጣን አማን “ችግኝን በመትከል አከባቢን ማሳመር ፈጣሪ ያዘዘን ተግባር ነው” ብለዋል፡፡

የሃይማኖት ተቋማት  በሰላም ግንባታ፣ በማህበራዊ ስራዎች እንዲሁም በልማት ስራዎች ላይ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቀናአ ያደታ ናቸው፡፡

አክራሪ ሃይማኖተኝነት፣ አክራሪ ብሔርተኝነት ለማንም የማይጠቅም በመሆኑ ምዕመናኖቻቸውን በማስተማር እንዲህ ዓይነት በጎ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ የድርሻቸውን እንዲወጡ ማሳሰባቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.