Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከገጠማት ፈተና እንድትወጣ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን መቆም አለበት – የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከገጠማት ዘርፈ ብዙ ፈተና ለመውጣት በምታደርገው ትግል ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን መቆም አለበት ሲሉ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ ተናገሩ።

የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባዔ መካሄድ ጀምሯል፡፡

በጉባዔው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ፥ ኢትዮጵያ ከገጠማትን ዘርፈ ብዙ ውጣ ውረድ እና ፈተና ለመውጣት መተባበር እና መደማመጥ የሚጠይቅበት ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡

“የተጀመረውን ትብብራችንንም አጠናክረን መቀጠል አለብን” ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ከጫፍ ለማድረስ እና በፅናት ለማሸነፍ ሁሉን አቀፍ ትግል ማድረግ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

ካለው የመልማት ፍላጎት እና የተፈጥሮ ሃብት፣ የጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ ፣ በኢትዮጵያ ጠንካራ መንግስት መኖር እና ጠንካራ ሀገር መሆንን በስጋት የሚመለከቱ ኃይሎች መበራከት እና ተመሳሳይ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ ችግሮች እያጋጠሙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የውጭ ጠላቶች ከሀገር ውስጥ ባንዳዎች ጋር በመተባበር ዘር እና ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሀገራችን አንድነት እየተፈታተኑ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የያዘውን ሀገራዊ አንድነት የማስጠበቅ ጉዞ አብዛኛው ሕዝብ በሙሉ ልብ እየደገፈው እንደሚገኝ ጠቁመው አሁንም ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ የክልሉ መንግስትን የ2014 በጀት ዓመት የ11 ወራት የልማት እና የመልካም አስተዳደር የዕቅድ አፈፃፀም ለምክር ቤቱ እያቀረቡ ነው፡፡

በምንይችል አዘዘው
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.