Fana: At a Speed of Life!

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች የባለሞያዎች ኮሚሽን አባላት ከመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያዩ መሆኑን መንግስት ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች የባለሞያዎች ኮሚሽን አባላት በአዲስ አበባ ከመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና አግባብነት ካላቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ላይ መሆናቸውን መንግስት ገለፀ።

በጉዳዩ ላይ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ አውጥቷል።

የመግለጫው ሙሉ ቃልም እንደሚከተለው ቀርቧል፦

የተባበሩት መንግስታት የሰብዐዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ በተለይም በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል በተከሰተው ግጭት አውድ ውስጥ የደረሱ የሰብዐዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲያጣራ ያቋቋመው ዓለም ዓቀፍ የሰብዐዊ መብቶች የባለሞያዎች ኮሚሽን ከአገራችን ጋር የትብብር እድልን አስመልክቶ ውይይት ለማድረግ በአዲስ አበባ ይገኛሉ።

የተባበሩት መንግስታት የሰብዐዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ በተለይም በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል በተከሰተው ግጭት አውድ ውስጥ የደረሱ የሰብዐዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጣራ የባለሞያዎች ኮሚሽን አቋቁሟል። የኢፌዲሪ መንግስት ይህ ኮሚሽን የተቋቋመበት ሂደት እና የተሰጠው ሃላፊነት ግልፅነት የጎደለው፣ ተገቢ ያልሆነ የፖለቲካ ቅኝት ያለው እና ከዚህ ቀደም የተባበሩት መንግስታት የሰብዐዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ጽ/ቤት እና የኢትዮጵያ የሰብዐዊ መብቶች ኮሚሽን በጥምረት ያደረጉትን የሰብዐዊ መብት ጥሰት ምርመራ እንዲሁም የዚህም የጥምር ምርመራ ቡድን ምክረ ሃሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በተገቢው መልኩ ታሳቢ ያደረገ እንዳልሆነ በመጠቆም ተቃውሞውን ገልፆ እንደነበር ያታወሳል።

በዚህም መሠረት መንግስት ከዚህ ኮሚሽን ጋር እንደማይተባበር ገልጾ እንደነበር ይታወሳል። ሆኖም ከኮሚሽኑ አባላት እና ከሌሎች ባላድርሻ አካላት ጋር ከዚህ ቀደም በተደረጉ ውይይቶች በተ.መ.ድ. የሰብዐዊ መብቶች ምክር ቤት የተቋቋመው ኮሚሽን ሃላፊነቱን ሲወጣ የመንግስትን መሠረታዊ አቋም ባገናዘበ እንዲሁም የአለም አቀፍ የሰብዐዊ መብት ስርዐት የብሄራዊ የህግ ስርዐቱ ደጋፊ እና ሟሟያ ሆኖ መታየት እንዳለበት አፅኖት የሚሰጠው የአሟይነት መርህ (principle of complementarity) ባከበረ፣ ተገቢነት ከሌላቸው የፖለቲካ ፍላጎቶች በነፃ፣ የተባበሩት መንግስታት የሰብዐዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ጽ/ቤት እና የኢትዮጵያ የሰብዐዊ መብቶች ኮሚሽን በጥምረት ያደረጉትን ምርመራ የማይደግም እና መንግስት ተጠያቂነትን ለማስፈን እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችን በማያስተጓጉል መንገድ የሚንቀሳቀስ ከሆነ በዝርዘር የእንቅስቃሴ አቅጣጫዎች ማዕቀፍ(modalities of engagement) ላይ መሰማማት ከተቻለ ከኮሚሽኑ ጋር የመተባበርን ጉዳይ መልሶ የማጤን እድል እንደሚኖር ተገልፆል። በዚህም መሠረት በጄኔቫ የተጀመሩ ውይይቶችን ለመቀጠል የባለሞያዎቹ ኮሚሽን አባላት በአዲስ አበባ ከመንግስት የስራ ሃላፊዎችን እና አግባብነት ካላቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ላይ ይገኛሉ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.