Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው የመረጃ ጦርነት በሳይበር ደህንነትና ሌሎችም ተቋማት የጋራ ጥረት እየተመከተ ነው- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው የመረጃ ጦርነት በሳይበር ደህንነትና ሌሎችም ተቋማት የጋራ ጥረት እየተመከተ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሣ÷ መንግሥት ጦርነቱን ለመመከትና ሕግ ለማስከበር ብርቱ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያስረዱት።

ቴክኖሎጂን በመጠቀምና ትክክለኛ ፈጣን መረጃን ወደ ሕዝብ በማድረስ የመረጃ ጦርነቱን ለመመከት ስልት ተነድፎ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ጠላቶች በሀሰተኛ መረጃ ሕዝቡን ለመከፋፈል የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፥ የመረጃ ጦርነቱ አገር ለማፍረስ ከፍተኛ ገንዘብ ተመድቦለት በተቀናጀ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው የመረጃ ጦርነት በሳይበር ደህንነት ተቋማትና በሌሎችም የጋራ ጥረት እየተመከተ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

መንግሥት የጠላትን የመረጃ ጦርነት ለመመከት ተቋማትን በማጠናከር ላይ መሆኑን ጠቁመው፥ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነትን የመሳሰሉ የመረጃ ደህንነት ተቋማት በመቀናጀት መልኩ በልዩ ትኩረት እየሠሩ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የመረጃ ትክክለኛነትን ማጣራት፣ ለሕዝብ ፈጣን መረጃዎችን ማድረስና አጀንዳ መቅረፅ ላይ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ የመረጃ ጦርነቱን በመመከት ሂደት የመገናኛ ብዙሃንም የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፥ ኢትዮጵያ የተከፈተባትን የተቀናጀ ግራጫ ጦርነት እየተፋለመች መሆኗን መግለፃቸው ይታወሳል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.