Fana: At a Speed of Life!

ዳያስፖራው ሀገራዊ ምክክሩ ፍሬያማ እንዲሆን የበኩሉን ሚና እዲወጣ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዳያስፖራው ማህበረሰብ ሀገራዊ ምክክሩ ፍሬ እንዲያፈራ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ጥሪ አቀረበ፡፡

“በሀገራዊ ምክክሩ የዳያስፖራው ሚና እና የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ” በሚል መሪ ሀሳብ የምክክር መድረክ በአዲስ አባበ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመርሐ ግብሩ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር መሀመድ ኢድሪስ እንደገለጹት÷ ሀገራዊ ምክክሩ ነፃና ገለልተኛ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ዳያስፖራው ኃላፊነቱን በአግባቡ በሚወጣበት መልኩ ምክክር ማድረግ አስፈልጓል፡፡

ሀገራዊ ምክክሩ ፍሬያማ እንዲሆን ዳያስፖራው የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ዳያስፖራው ማህበረሰብ “እኔም ለሀገሬ፣ ሀገሬም ለኔ” በሚል መሪ ቃል የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አብራርተዋል ።

ድንበር ተሻጋሪ አንድነትን የሚያጠናክር ስራ እየተሰራ ነው ያሉት ምክትል ዳይሬክተር ÷እስካሁን ከ800 በላይ በአካልና በቪዲዮ አንድነትን የሚያጠናክሩ ኮንፈረንሶችን ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው÷ ከዳያስፖራው “ከኢድ እስከ ኢድ” እና “ታላቁ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት” እቅዶችን ከማሳካት አንጻር ቀላል የማይባል ውጤት ማምጣት ተችሏል ነው ያሉት።

በዚህም ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መነቃቃት በማምጣት ረገድ ዳያስፖራው ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡

የሀገራዊ ምክክሩ ላይ የዳያስፖራው ሚና እና የሀገራት ተሞክሮን በተመለከተ የሚደረገው ምክክር የሀገርን ችግር በራስ ለመፍታት እንዲያስችል ያለመ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል፡፡

በይስማው አደራው እና አወል አበራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.