Fana: At a Speed of Life!

ከመጋቢት 10 ጀምሮ አዲስ ፓስፖርት በ1 ወር ጊዜ ውስጥ መሰጠት ይጀምራል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ከመጋቢት 10 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ አዲስ ፓስፖርት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ መስጠት ሊጀምር መሆኑን ገለጸ።
 
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጅብ ጀማል እንደገለጹት፥ ከዚህ ቀደም አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት ሁለት ወር ከ15 ቀን በላይ ይወስድ የነበረው ጊዜ ወደ አንድ ወር ዝቅ እንዲል ተወስኗል።
 
በአዲሱ አሰራር መሰረት ፓስፖርት በአስቸኳይ ለማውጣት እስከ አምስት ቀን ብቻ እንደሚወስድም ተናግረዋል።
ካለፈው ዓመት የካቲት ወር ጀምሮ በፓስፖርት ወረቀት እጥረት ምክንያት የአዲስ ፓስፖርት መስጫ ጊዜ ከአንድ ወር ወደ ሁለት ወር ከ15 ቀን መራዘሙ ይታወሳል።
 
በአሁኑ ሰዓት ኤጀንሲው ከ270 ሺህ እስከ 300 ሺህ ፓስፖርት እንዳለው የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፥ በቀጣይ 500 ሺህ ፓስፖርት ለማስገባት ስምምነት መደረሱን አንስተዋል።
 
ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት ተመዝግበው ከሁለት ወር እስከ ሶስት ወር የሆናቸው 90 ሺህ ተገልጋዮች እየተጠባበቁ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
 
ኤጀንሲው መሰል ችግሮችን ለማስወገድም ከፊታችን መጋቢት 10 ቀን ጀምሮ አዲስ አሰራር ተግባራዊ ያደርጋል ነው ያሉት።
 
በሌላ በኩል በአስቸኳይ ፓስፖርት ሲያወጡ የነበሩ ሰዎች የገንዘብ ጭማሪ ተደርጎብናል በሚል ሲያቀርቡት የነበረው ቅሬታ በወረቀት እጥረት ምክንያት የተከሰተ መሆኑንም አስረድተዋል።
 
እንዲሁም የፓስፖርቱ የገጽ መጠን በእጥፍ መጨመሩን ጠቅሰው፥ በአዲስ መልክ በሚጀመረው የፓስፖርት አሰጣጥ ስርዓት ችግሩ ይቀረፋል ብለዋል።
 
በአስቸኳይ ፓስፖርት ለማውጣት የሚጠየቁ መስፈርቶችን ያላሟሉ እና መደበኛውን ፓስፖርት ያለአግባብ ሲሰጡ የነበሩ ሰራተኞች እንደነበሩም ተመላክቷል።
 
በዚህም ያለአግባብ መስፈርቱን ላላሟሉ እና ለውጭ ዜጎች ፓስፖርት የሰጡ 10 ሰራተኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ነው የተናገሩት።
 
በተደረገው የማጣራት ስራ ሰራተኞቹ ከውጭ ዜጎቹ ከ5 ሺህ ዶላር በላይ መቀበላቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፥ 77 የሚሆኑ ፓስፖርቶች በህገ ወጥ መልኩ ተሰርተው መገኘታቸውንም አንስተዋል።
 
ከዚህ ጋር ተያይዞም ፓስፖርቶቹ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ለኢንተርፖል ማሳወቅ እና ሰዎቹን ተጠያቂ የማድረግ ስራ መሰራቱንም ጠቅሰዋል።
 
በዙፋን ካሳሁን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.