Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የምታዘጋጀው የመጀመሪያው የበይነመረብ አስተዳደር ጉባዔ የፊታችን ሐምሌ 28 እንደሚካሄድ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የምታዘጋጀው የመጀመሪያው የበይነመረብ አስተዳደር ጉባዔ ሐምሌ 28 ቀን 2014 እንደሚካሄድ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሐምሌ 28 ቀን 2014 በአዲስ አበባ የሚካሄደውን ጉባዔውን አስመልክተው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው÷ ኢትዮጵያ የምታዘጋጀው የመጀመሪያው የበይነመረብ አስተዳደር ጉባዔ በአካል እና በኦንላይን ጥምረት እንደሚካሄድ ጠቁመው÷ ይህም የ 17ኛው ዓለም አቀፍ የበይነመረብ አስተዳደር ጉባዔ አካል መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ጉባዔው÷ የበይነ መረብ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥቅሞች፣ ተመጣጣኝ እና ትርጉም ያለው የበይነመረብ ተደራሽነት፣ የበይነመረብ ተደራሽነት እንደ መሰረታዊ መብት በሚሉት ጉዳዮች ላይ እንደሚወያይ አብራርተዋል፡፡
በይነ መረብ ከጥቅሙ ባሻገር ከመረጃ መረብ ወንጀሎች፣ ከጥላቻ ንግግሮች፣ የሀሰትና የተዛቡ ዜናዎች ስርጭት አኳያ የተለያዩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አሉታዊ ጎኖች እንዳሉት መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ጉባዔው ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመት ለምታስተናግደው 17ኛው ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባዔ መሰረት የሚጥል መሆኑም ተገልጿል፡፡
የቀጣዩ ዓመት ጉባዔ የኢትዮጵያን ገፅታ ለመገንባት፣ ኢትዮጵያ እየሠራች ያለውን ሥራ ለዓለም ለማሳየት፣ የኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካን ተሰሚነት ለማሳደግ፣ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ትስስር ለመፍጠር እንዲሁም ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ትልቅ አስተዋፅዖ አለው ብለዋል ዶክተር በለጠ በመግለጫቸው፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.