Fana: At a Speed of Life!

በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አኩሪ ድል ላስመዘገቡት አትሌቶች እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚደርስ ሸልማት ተበረከተ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አኩሪ ድል ላስመዘገቡ አትሌቶች ከ50 ሺህ ብር እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚደርስ ሸልማት ተበረከተ፡፡

በአሜሪካ ኦሪገን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተመዘገበውን አኩሪ ድል በማስመልከት የአትሌቶች የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል መርሐ-ግብር በብሔራዊ ቤተ-መንግስት እየተካሄደ ነው፡፡

በመርሐ – ግብሩ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ  ዘውዴን ጨምሮ  የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተግኝተዋል፡፡

በመድረኩ በ18 ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አኩሪ ድል ላስመዘገቡ አትሌቶች  እና ሌሎች የልዑካን ቡድን አባላት ከ50 ሺህ ብር እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚደርስ ሽልማት ተበርክቷል፡፡

በሻምፒዮናው ለተሰንበት ግደይ በ10 ሺህ ሜትር የመጀመሪያውን ወርቅ በማስገኘቷ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር  እና በ5 ሺህ ሜርት ላሳየችው ውጤታማ የቡድን ሥራ 500 ሺህ ብር በድምሩ የ2 ሚሊየን ብር ተሸላሚ ሆናለች፡፡

በተጨማሪም በሴቶች ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘችው አትሌት ጎይተቶም ገብረ ሥላሤ  እና በወንዶች ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘው ታምራት ቶላ እያንዳንዳቸው የ1 ሚሊየን 750 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

በ1 ሺህ 500 ሜትር የብር ሜዳሊያ እና በ5 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘቸው ጉዳፍ ጸጋይ በልዩ ሁኔታ የ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ተሸላሚ ሆናለች፡፡

በወንዶች ማራቶን ሁለተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ የብር ሜዳሊያ ያስገኘው ሞስነት ገረመው 1 ሚሊየን ብር፣ በ3 ሺህ መሰናክል የብር ሜዳሊያ ያስገኘቸው  ወርቅውሃ ጌታቸው 1 ሚሊየን ብር እንዲሁም በ3 ሺህ መሰናክል   የብር ሜዳሊያ ላስገኘው ለሜቻ ግርማ  የ1 ሚሊየን ብር  ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.