Fana: At a Speed of Life!

ምስጋና ለበለጠ ሥራና ትጋት አስፈላጊ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል – የእስልምና ሃይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምስጋና ለበለጠ ሥራ እና ትጋት አስፈላጊ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥልና ሊለመድ ይገባል ሲሉ የእስልምና ሃይማኖት አባቶች ተናገሩ፡፡

“ኢትዮጵያ ታመስግን” የምስጋና መርሐ ግብር በተለያዩ መስጂዶች ተካሂዷል።

በአዲስ አበባ አል-አቅሳ መስጂድ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶች ፥ ምስጋና በእስልምና እምነት ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን በመናገር በምስጋና ተጨማሪ ጸጋ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

የእስልምና እምነት መምህሩና የአል-አቅሳ መስጂድ ዋና ኢማም ሸኽ ሰኢድ አሕመድ ሙስጠፋ እንደተናገሩት ፥ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በአያሌ ፈተናዎች ውስጥ ማለፏን ጠቅሰው በፈተና ውስጥም ፈጣሪን ማመስገን ይገባናል ነው ያሉት፡፡

ሸኽ ሰኢድ እንዳሉት ፥ ምስጋና ከልብ በሆነ ስሜት በተግባር ሲገለጽ ፍሬያማ ይሆናል፡፡

ምስጋና ፈጣሪ የሰጠንን ነገር በማካፈል እንደሚገለጽ በማስረዳት ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ እውቀት ያለው በእውቀቱ ይህንኑ ማድረግ ይችላል ብለዋል፡፡

ሁሉም ሰው ቀና ነገር ከሰራ፣ ከተረዳዳ፣ ከተዛዘነና ከተደጋገፈ ምስጋና ሊቸረው እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡

የሀገራችን አትሌቶች ያስመዘገቡት ውጤት የመተባበርና የአንድነት ውጤት መሆኑን በመገንዘብ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባልም ነው ያሉት።፡

ሁሉም በተሰማራበት መስክ ተባብሮና ተደጋግፎ ከሰራ ውጤት ማምጣት እንደሚቻልም ነው የተናገሩት፡፡

የአል-አቅሳ መስጂድ አስተዳዳሪ ሸኽ አብዱልመናን ሁሴን በመርሐ ግብሩ ምስጋናን የተመለከቱ ትምህርቶች (ቁጥባ) መሰጠታቸውን ተናግረው ፥ ምስጋና ለበለጠ ሥራ እና ትጋት አስፈላጊ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥልና ሊለመድ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የኃይማኖት ትምህርት የሚከታተለው ወጣት ጀማል ጠሃ በበኩሉ ፥ በእምነት ውስጥ ሁለት ነገሮች በጣም አስፈላጊ መሆናቸውን በመናገር እነሱም ትዕግስትና ምስጋና ናቸው ብሏል፡፡

በአንድነት ብዙ ነገሮችን በመታገስ ችግሮችን አልፈን አትሌቶቻችን ላስመዘገቡት ድል በመብቃታችን ልናመሰግን ይገባልም ነው ያለው።

ኢትዮጵያውያን አንድ ከሆንን ሁሉም ቦታዎች ላይ አሸናፊዎች እንሆናለን ፤ ለዚህ ደግሞ የአትሌቶቻችን ድል ማሳያ ነው ሲሉ የእምነቱ ተከታዮች ተናግረዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.