Fana: At a Speed of Life!

ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢ.ፌ.ዴ.ሪ አገር መከላከያ ምክትል የኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር ተወያዩ።

በጄኔራል ብርሃኑ ጁላ የተመራ የልዑካን ቡድን በሱዳን የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ መሆኑን በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል።

በጉብኝታቸውም በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ላይ የተቃጣውን ግድያ ሙከራ አስመልክቶ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ መልዕክትን አድርሷል።

በጄኔራል ብርሃኑ ጁላ የተመራ የልዑካን ቡድኑ በጉብኝቱ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋርም ተወያይተዋል።

በተጨማሪም የሱዳን መከላከያ ሚኒስትር ጄኔራል ጀማለዲን ኦማር እና የሱዳን ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ኡስማን መሃመድ ጋር ውይይቶችን በማካሄድ በቅርቡ በሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ የተቃጣው የግድያ ሙከራ እንደሚያወግዙ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ባለው አስቸጋሪ ሁኔታ ከሱዳን ጎን እንደምትቆም ያረጋገጡ ሲሆን፥ የሱዳን ሰላምና ብልጽግና የኢትዮጵያ እንደሆነ ሁሉ የሱዳንም ችግር እንዲሁ የኢትዮጵያ እንደሆነ አስምረውበታል።

በሱዳን በኩልም ኢትዮጵያና ሱዳን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ያላቸውና ኢትዮጵያ ለሱዳን ችግር ፈጥና የምትደርስ መሆኗን እና ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በሱዳን የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም የነበረው የሰላም ድርድር ውጤታማ እንዲሆን የተጫወቱትን ቁልፍ ሚና አስታውሰዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሱዳንን ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቅ በመሆኑ ድጋፍ እንዳላቸው ተገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.