Fana: At a Speed of Life!

ተከስቶ የነበረው የዶሮ በሽታ በቁጥጥር ሥር በመዋሉ ሕብረተሰቡ ዶሮና እንቁላል መመገብ ይችላል – ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ተከስቶ የነበረው የዶሮ በሽታ በቁጥጥር ሥር በመዋሉ ሕብረተሰቡ ያለምንም ስጋት ዶሮና እንቁላል መመገብ እንደሚችል የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ እና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ ጉዳዩን አስመልክቶ በጋራ ለኢዜአ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ ፥ ባሳለፍነው ሰኔ ወር መባቻ በቢሾፍቱና በምዕራብ አዲስ አበባ የተከሰተው የዶሮ በሽታ ወረርሽኝ በዶሮ እርባታ ቦታዎች ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል።

በሽታው እንደተከሰተ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ሌሎች ባለድርሻ ተቋማት የተውጣጣ ግብረ-ኃይል ተሰማርቶ የበሽታውን ሥርጭት የመግታት አፋጣኝ ምላሽ መውሰዱንም ነው የገለጹት።

በወቅቱ ለዶሮ እርባታ አገልግሎት ከውጭ የሚገባው የለማ እንቁላልና ዶሮና የዶሮ ውጤቶች ዝውውር ባለበት እንዲገታ የጥንቃቄ መመሪያዎች ለሚመለከታቸው አካላት መተላለፉን አስታውሰዋል።

በተጨማሪም ዶሮና እንቁላል አመጋገብ ላይ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ መተላለፉን ገልጸው፤ በሂደትም የጥንቃቄ መመሪያዎች እየተሻሻሉ መሄዳቸውን ተናግረዋል።

በሽታውን ለመከላከል በተከናወኑ ተግባራት ምክንያት በሽታውን በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉንም ገልጸዋል።

አሁን ላይ ምንም አይነት የበሽታ ስጋት ባለመኖሩ ሕብረተሰቡ ዶሮና እንቁላል ያለስጋት በማብሰል እንዲጠቀም ፤ ዶሮ አርቢዎችም በሙሉ አቅማቸው ዶሮ በማርባት ለገበያ እንዲያቀርቡ መወሰኑን ተናግረዋል።

ሆኖም በዶሮ እርባታ የተሰማሩ ዜጎች በማንኛውም ጊዜ የሚያደርጉትን ‘ባዮ-ሴኪዩሪቲ’ የተሰኘውን የዶሮ እርባታ ጥንቃቄ ሥርዓትን ባጠናከረ አግባብ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው፤ በሽታው ከተከሰተ ጀምሮ በሰው ጤና ላይ ጉዳት ያስከተለው ጉዳት ካለ ለመለየት ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድን ተዋቅሮ በተጠናው ጥናት በሰው ላይ ምንም ጉዳት አለማድረሱን ተናግረዋል፡፡

በወረርሽኙ ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዶሮዎች መሞታቸውን ጠቅሰው፤ በዶሮና የዶሮ ውጤቶች እንቅስቃሴ ላይ እገዳ መጣሉ ደግሞ ዘርፉ ላይ ጉዳት ማድረሱን አንስተዋል፡፡

እንደ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ ገለጻ ፥ ወረርሽኙን ለመከላከል የተከናወኑ ተግባራት የዶሮ እርባታ ሥርዓትን ማሻሻልና የአርቢዎችን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ትምህርት ሰጥቷል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.