Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የስንዴ ልማት ፕሮግራም በምግብ ራስን ለመቻል ግልፅ ራዕይ አስቀምጦ ከተሰራ እንደሚሳካ የሚያሳይ ምሳሌ ነው – ዶ/ር ፍጹም አሰፋ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እየተገበረችው የምትገኘው ብሄራዊ የስንዴ ልማት ፕሮግራም በምግብ ራስን ለመቻል ግልፅ ራዕይ አስቀምጦ ለስኬቱ የሚያስፈልገውን ፖሊሲ መተግበር እና ሀብት ማዋል ከተቻለ ማሳካት እንደሚቻል የሚያሳይ ምሳሌ መሆኑን የኢፌዴሪ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋ ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሯ ከሲኤን ኤንጋር በነበራቸው ቆይታ፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅና የምግብ ዋጋ መናር እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ላይ ተፅዕኖው የጎላ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተዳክሞ የነበረው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከጉዳቱ ሳያገግም የሩሲያና ዩክሬን ግጭት ወዳስከተለው ሌላ ቀውስ ውስጥ ገብቷል ያሉት ሚኒስትሯ÷ በዋነኛነትም የነዳጅና የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት መስተጓጎል እየጨመረ ለመጣው የዋጋ ንረት የጎላ አስተወፅኦ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት የቅርብ ጊዜ ክስተት ሳይሆን በዘመናት የምርታማነት እና ተወዳዳሪነት ማነስ የተነሳ ሲንከባለል አሁን ያለበት ደረጃ የደረሰ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
ችግሩን ከስሩ ለመቅረፍም መንግስት የአሥር ዓመት የልማት መሪ ዕቅድ ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ያለው አለመረጋጋት እና ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ጫናዎች ፈታኝ ቢሆኑም እነዚህን ሁሉ ከግምት ባስገባ መልኩ የተዘጋጀው መሪ ዕቅድ ችግሮቹን በተሻለ መልኩ ለመሻገር እደሚያግዝ አብራርተዋል፡፡
በዋነኛነትም በግብርና እና ግብርና መር ኢኮኖሚ ላይ በሰፊው በመስራት ምርታማነትን ለማሳደግ መሪ እቅዱ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አንስተዋል፡፡
የበጋ የስንዴ መርሐ ግብርን በመጠቀም የዝናብ ወቅትን ብቻ በመጠበቅ ይከናወን ከነበረው የግብርና ሥርዓት በመውጣት በመስኖ የታገዘ የስንዴ ልማት በተሰራው ስራ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ቶን ስንዴ ማምረት መቻሉን አስረድተዋል፡፡
ይህ የተቀናጀ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ስርዓትም የተዳከመውን ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ያግዛል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ እየተገበረችው የምትገኘው ብሄራዊ የስንዴ ልማት ፕሮግራም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የዋጋ ንረትን ለመቋቋም ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ዓለማችን አሁን ላይ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በኮቪድ- 19 እና በተለያዩ አስደንጋጭ ክስተቶች እየተናጠች እንደምትገኝ ጠቁመው፥ የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት መቀስቀስ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ የከፋ እንዳደረገው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.