Fana: At a Speed of Life!

በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነው የህዝብን ሃብት የሚመዘብሩ አመራሮች እና ሰራተኞችን አንታገስም-አቶ ደስታ ሌዳሞ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነው የህዝብን ሃብት የሚመዘብሩ አመራሮችና ሰራተኞችን አንታገስም ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
አቶ ደስታ በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የ2014 በጀት ዓመት አፈፃፀም እና የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ግምገማን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ÷ በተጠናቀው በጀት ዓመት በዓመቱ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ክልሉ በትኩረት ሲሰራ እንደነበር አንስተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ክልሉ ካለው አቅም አንፃር በቂ ምርት አግኝቷል ማለት እንደማይቻል ነው የጠቆሙት፡፡
በቀጣይም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና ክልሉ በምግብ እራሱን ከመቻል አልፎ ለሀገር የበኩሉን እንዲያበረክት የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ከፌዴራል መንግስት ጋር የግብርና ግብዓቶችን ማግኘት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ክልሉ በ2014 በጀት ዓመት ካከናወናቸው ተግባራት አንዱ በክልሉ የስራ እድል ያላገኙ ስራ አጦችን ወደ ስራ ማስገባት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷በዚህም 92 ሺ ወጣቶችን የቋሚ ስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ከነዚህ መካከልም አብዛኞቹ ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡
ከስራ እድል ፈጠራው ጋር በተያያዘ በመንግስት መስሪያ ቤቶች መቀጠር እንጂ ስራ መፍጠር የሚፈልግ ወጣት መጥፋቱ አንዱ ፈተና እንደነበር ጠቁመው÷ ይህን አስተሳሰብ ለመቀየርና ስራ ፈጣሪ ወጣት ለመፍጠር ስልጠና መሰጠቱን አንስተዋል።
በቀጣይ የክልሉ መንግስት ትኩረት ከሚያደርግባቸው ዘርፎች አንዱ ሌብነትና አገልግሎት አሰጣጥን ማስተካከል መሆኑን አቶ ደስታ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነው የህዝብን ንብረት የሚመዘብሩ ሰራተኞችን ከስራቸው በማንሳት ስራ ፈላጊዎችን በነሱ ቦታ እንተካለን፤ መሰል ድርጊት በሚፈጽሙ አመራሮች እና ሰራተኞች ላይ የሚወሰደው የህግ እርምጃም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ከዚህ ባለፈም የክልሉን ገቢ በማሳደግ የሚገኘውን ገቢ በቁጠባና ያለብክነት በመጠቀም የክልሉን የመሰረተልማት ጥያቄ ለመመለስ በታማኝነትና በትጋት ይሰራል ነው ያሉት።
በጥላሁን ይልማና ደብሪቱ በዛብህ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.